ሶስተኛውን የፊት ገጽታ በንቅለ ተከላ ያገኘው ግለሰብ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 09፣ 2010፣(ኤፍ.ቢ.ሲ) ጀሮሜ ሀሞን የተባለ ፈረንሳዊ ግለሰብ ለሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ የፊት ንቅለ ተከላ የቀዶ ህክምና ከተደረገለት ሶስት ወራት በኋላ ጤንነት እንደተሰማው ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

ጀሮሜ ሀሞን የተባለው ፈረንሳዊ ቀደም ሲል በንቅለ ተከላ የተሰራለት ፊቱ ለጉንፋን በሽታ የተሰጠው መድሃኒት በፈጠረበት የጤና እንከን ባለፈው ዓመት እንደገና እንደተነሳ ነው የተገለጸው።

 የ43 ዓመቱ ጀሮሜ ሀሞን ተስማሚ ፊት ለጋሽ እስኪገኝ ድረስም ፓሪስ በሚገኘው ጊወርጊስ ፖምፒዶ ሆስፒታል ማየት፣ መስማትና መናገር ሳይችል ለሁለት ወራት እንደቆየም ነው ዘገባው የሚያስረዳው።

ግለሰቡ የመጀመሪያው የፊት ንቅለ ተካላ ሲደረግለትም ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት የነበረ መሆኑ ታውቋል።

ቀደም ሲል ጀሮሜ ሀሞን የፊት ገጽታውን የሚያበላሹ እባጮች በፊቱ ላይ በመውጣታቸው ለዚህ ችግር እንደተዳረገም በዘገባው ተጠቅሷል።

በዚህም በፈረንጆቹ 2010 የተሳካ የፊት ንቅለ ተከላ የተካሄደለት ሲሆን፥ በ2015 ለጉንፋን በሽታ የተሰጠው መድሃኒት በፊቱ ላይ ባሳደረበት ተጽዕኖ እንደገና ፊቱ እንዲነሳ አድርጎታል ተብሏል።

ሀሞን የ43 አመት ጎልማሳ ሲሆን፥ አዲሱን ፊቱን የለገሰው ሰው የ22 ዓመት ወጣት በመሆኑ እንደገና የወጣትነት ገጽታን እላበሳለሁ ሲልም ተናግሯል ተብሏል።

የመጀመሪያው የፊት ንቅለ ተከላ በሰሜን ፈረንሳይ በ2005 የተደረገ ሲሆን፥ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 ያህል ተመሳሳይ ስራዎች እንደተሰሩ ዘገባው ያስረዳል።

 

 

 

 

 

ምንጥ፦ ቢቢሲ

 

የተተረጎመና የተጫነው፦ እንቻለው ታደሰ