እንግሊዛዊው ለ160 ኪሎ ሜትር የባቡር ጉዞ ከተጠየቀው ገንዘብ ባነሰ ዋጋ ተሽከርካሪ ገዝቷል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 9 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) እንግሊዛዊው የ27 አመት ወጣት የቅርብ ጓደኛውን ለመጠየቅ የመረጠው መንገድ ትንሽ ለየት ያለ ሆኗል።

ወጣቱ ጓደኛውን ለመጠየቅ ከለንደን ወደ ብሪስቶል ከተማ ለማምራት ወደ ባቡር ጣቢያ ያመራል።

ይሁን እንጅ ባቡር ጣቢያ ከደረሰ በኋላ ለ160 ኪሎ ሜትሩ መንገድ 218 ፓውንድ መክፈል እንዳለበት ይነገረዋል።

በዚህ ሳቢያም ሌላ አማራጭ ፍለጋ ሲያማትር፥ የሚሸጡና ስሪታቸው ቆየት ያሉ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች መኖራቸውን ከአንድ የኦንላይን ግብይት ማስታወቂያ ላይ ይመለከታል።

በዚህ ሂደትም ስሪቷ የ19 97 የሆነችና አነስተኛ ሆንዳ ሲቪክ የምትሸጥ ተሽከርካሪን ከአንድ ወይዘሮ ያገኛል።

የተሽከርካሪዋ ዋጋ ደግሞ ቶም ለባቡር ከተጠየቀው ክፍያ አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ነበር፤ 81 ነጥብ 38 ፓውንድ ዋጋ ሲኖራት ለጉዞው ደግሞ አጋዥ ነበረች።

ቶምም በከፍተኛ ገንዘብ ወደ ጓደኛው ከማምራት ይልቅ ይችን ተሽከርካሪ መግዛት የተሻለ አማራጭ በመሆኑ ግዥውን ይፈጽማል።

ቶም ተሽከርካሪዋን ለመግዛት፣ ካልተወራረደ የደርሶ መልስ የመንገድ ክፍያና ለነዳጅ ያወጣውን ወጪ ጨምሮም አጠቃላይ 206 ፓውንድ ወጪ አድርጓል።

ይህ ደግሞ ለባቡር ትኬት መክፈል ከሚጠበቅበት 218 ፓውንድ አንጻር አነስተኛ ነበር፤ የባቡሩ ትኬት ለአንድ ጉዞ ብቻ የሚያገለግል ሲሆን ተሽከርካሪዋ ግን ከጉዞው በኋላም የግሉ ሆና ትቀጥላለች።

ይህ መሆኑ ደግሞ ለቶም አስደሳች ሆኖለታል በአነስተኛ ወጪ ወዳጁን ጠይቆ መመለስና ተሽከርካሪዋንም የራሱ ማድረጉ ለእርሱ ከባቡሩ ጉዞ ይልቅ የተሻለው ነበር።

“ካለው ሁኔታ አንጻር ከታየ የተሽከርካሪዋ ዋጋ ውድ ነው” የሚለው ቶም፥ “ቁም ነገሩ የመኪናዋ ዋጋ ከልክ በላይ ከተጋነነው የባቡር ጉዞ ዋጋ አንጻር ሲታይ” መሆኑንም ይገልጻል።

እናም ወጪ ከማብዛት መሰል መንገድ በመጠቀም ያሰቡትን ማሳካቱ የተሻለ መሆኑንም ይናገራል።

ቶም የፈለገውን ያገኘ ሲሆን፥ ተሽከርካሪዋን ሊሸጣት እንደሚችልም ይገልጻል፤ በሂደቱ ምናልባትም የተሻለ አትራፊ ሊሆን እንደሚችልም ይጠቅሳል።

 

 

ምንጭ፦ odditycentral.com