ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሰራ ጫማና ክራቫት ያደረገው ፓኪስታናዊ ሙሽራ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሰርጋቸውን እለት ለየት ለማድረግ እና ደምቆ ለመታየት የተለያዩ ወጣ ያሉ ተግባራትን ሲያከናወኑ በብዛት ይስተዋላል።

ፓኪስታናዊ ሳልማን ሻሂድም ከእነዚህ አንዱ ሲሆን፥ በሰርጉ ላይ ያደረገው ተግባርም ከአካባቢው አልፎ በዓለም ዙሪያ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል ነው የተባለው።

ከፓኪስታን የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት ሙሽራው ሳልማን ሻሂድ በሰርጉ እለት እጅግ ውድ የተባለ ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሰራ ጫማና ክራቫት ለብሶ ነው የሰርግ ስነ ስርዓቱ ላይ የታደመው።

ሙሽራው በአጠቃላይ በሰርጉ እለት ለለበሰው አልባሳት ብቻ ከ63 ሺህ የፓኪስታን ሩፒ በላይ ወጪ ማድረጉም ተነግሯል።

ሳልማን ሻሂድ በሰርጉ እለት የተጫማው ጫማ ከ320 ግራም ወርቅ የተሰራ ሲሆን፥ ለጫማው ብቻ 17 ሺህ የፓኪስታን ሩፒ ወጪ አድርጓል።

ስለ አለባበሱ የተጠየቀው ሳልማን፥ “ሁሌም የወርቅ ጫማ መጫማት ምኖቴ ነበር” ብሏል።

“ሰዎች ወርቅን አንገታቸው ላይ ወይም ደግሞ እንደ ዘውድ ጭንቅላታቸው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔ ደግሞ ሀብት ከሁሉም በታች መሆኑን እና ከእግራችን በታች መሆን እንዳለበት ለማሳየት ፈልጌ ነው ይህንን ያደረኩት” ሲልም ተናግሯል።

gold_s.jpg

ሳልማን ሻሂድ አለባበስ በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፆች ላይ ከተለቀቀ በኋላ በርካቶች እየተነጋገሩበት ሲሆን፥ ሙሽራው አንዲህ ከለበሰ ሙሽሪትስ ምን ለብሳ ይሆን የሚለው ጥያቄም የበርካታ አስተያየት ሰጪዎች ነበር።

ምንጭ፦ www.ndtv.com