የተራራማ ቦታዎች አፈር መሸርሸርና የአለቶች መጋለጥ በከባቢ አየር ውስጥ የበካይ ጋዝ መጠን እንዲጨምር ያደርጋል፦ ጥናት

አዲስ አበባ ሚያዚያ 05፣ 2010፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቀደም ሲል በአፈር መሸርሸር የተራቆቱ ተራራዎች ከከባቢ አየር ካርበንዳይ ኦክሳይድ ጋዝን በመሳብ በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን ክምችት ይቀንሳሉ የሚል አስተሳሰብ የበላይ እንደነበረ የጥናቱ ተመራማሪ ጆርዳን ኸሚንግወይ ይገልፃሉ።

አዲሱ ጥናት በተቃራኒው በአፈር መሸርሸር የተራቆቱ ተራራዎች በካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ የካርበንዳይ ኦክሳይድ መጠን እንዲጨምር እንደሚያደረጉ መረጋገጡ ነው የተገለጸው።

 ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶች ግን የተራራዎች አፈር መሸርሸርና የአለቶች መጋለጥ ከከባቢ አየር ካርበንዳይ ኦክሳይድ አየርን የሚስቡ እንደሆነ ነበር የሚታወቀው ተብሏል።

ይሁን እንጂ የተራራዎች አፈር መሸርሸርና የአለቶች መጋለጥ ወደ ከባቢ አየር ካርበንዳይ ኦክሳይድ የሚለቁ እንደሆነ አዲሱ ጥናት በሳይንስ ጆርናል ለህትምት እንደበቃም ታውቋል።

አዲሱ ጥናት የቀድሞው የአስተሳሰብ የበላይነትን የተራቆቱ ተራራዎችና የተጋለጡ አለቶች ካርበንዳይ ኦክሳይድን ከከባቢ አየር ይስባሉ የሚለውን ሀሳብ የሻረ እንደሆነ የጥናቱ ተመራማሪ ጆርዳን ኸሚንግወይ ተናግረዋል።

በተራቆቱ ተራራዎች ላይ በሚገኙ የአለት ስብርባሪ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን በአይን የማይታዩ ረቂቅ ተህዋስያን ሲመገቡና የንጥረ ነገሮች ውህደት ሲካሄድ የካርበንዳይ ኦክሳይድ ጋዝ ልቀቱ እንደሚፈጠር ተመራማሪው ተናግረዋል።

የአዲሱ የጥናት ውጤት የተገኘውም ተመራማሪዎቹ በአለም አቀፍ ደረጃ በአፈር መሸርሸርና በአለቶች መጋለጥ ታዋቂ በሆኑ የታይዋን ሰንሰለታማ ተራራዎች ላይ ባደረጉት ጥናት ነው ተብሏል።

በዚሁ ጥናት ተመራማሪዎቹ በወሰዱት የአፈር ናሙና ውስጥ ምንም ተፈጥሯዊ ካርበን እንዳለገኘበትም ተረጋግጧል ነው የተባለው።

 በነፋስ፣ በጸሀይና ጎርፍ ተራራዎች ሲሸረሸሩና አለቶች በተጋለጡ ቁጥር በአይን የማይታዩ ተህዋስያን ተፈጥሯዊ ካርቦኑን በመጠቀም በምትኩ ካርበንዳይ ኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር እንደሚለቁ ነው ጥናቱ ያመለከተው።

የትኛው አይነት ረቂቅ ተህዋስ ይህንን ተግባር እንደሚያከናውን በጥናቱ ያልተለየ ሲሆን፥ በተናጠል ተህዋሱን ለመለየት ተጨማሪ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተማራማሪዎች ተናግረዋል።

የካርበንዳይ ኦክሳይዱ አየር ልቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት የማይሆን ቢሆንም የተራራዎች መራቆትና የአለቶች መጋለጥ ለካርበንዳይ ኦክሳይዱ አየር መጨመር የራሱ እስተዋጽኦ እንዳለው ተመራማሪዎቹ አስረድተዋል።

 

 

 

 

 

ምንጭ፥ upi.com

 

የተተረጎመና የተጫነው፦ እንቻለው ታደሰ