ለሴት ልጃቸው የወንድ ስም የሰጡት ወላጆች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቤተሰቦች ስም ለማውጣት ብዙ ክርክሮች ያደርጋሉ ያለው ሚረር በፈረንሳይ ግን ከዚህ በተለየ ለሴት ልጃቸው የወንድ ስም በማውጣታቸው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተነግሯል።

ለህፃኗ ልጅ ቤተሰቦቿ “ሊያም” የሚል ስም ቢያወጡላትም ፍርድ ቤቱ ለሴት ልጅ የሚሆን ስም አይደለም ብሎ ማገዱ ነው የተነገረው።

 የልጅቱ ስም የህፃናትን ፍላጎት የሚፃረር እና በማህበራዊ ግንኙነት ላይ ትፅዕኖ ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ስሙን ሊያግደው እንደሚገባ አቃቤ ህጎች ተናግረዋል።

በተጨማሪም ስሙ ፆታዊ የሆኑ ብዠታዎችን ይፈጥራል ተብሏል።

ጉዳዩን የሚከታተለው ፍርድ ቤት የህፃኗ ቤተሰቦች አዲስ ስም እንዲያወጡ ማዘዙም ተገልጿል።

ሆኖም የህፃኗ ቤተሰቦች ልጃቸው ባውጡላት ስም እንድትጠራ እንደሚፈልጉና ለዚህም የህግ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የተናገሩ ሲሆን፥ የህፃኗን ጥምቀት( baptism) ማራዘማቸው ታውቋል።

በልጃቸው ስም ምክንያት ፍርድ ቤት የቆሙት ወላጆች ጉዳይ ለልጆች ስም ማውጣት ላይ ጥብቅ ስርዓት አላት በምትባለው ፈረንሳይ ያልተለመደ መሆኑ ተነግሯል።

ከዚህ በፊት በፈረንሳይ ኑታላ፣ ስትሮዎበሪ እና ማንሃታ የተሰኙ ስሞች ለልጆች ማውጣት መከልከሉ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ሚረር