ሳንድዊች ለሚስቱ አልገዛም ያለ ግብፃዊው ወጣት መጨረሻው ፍቺ ሆኗል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በግብፅ የ30 ዓመቷ ወጣት ሴት የ32 ዓመት ባሏን ካገባች 40 ቀን ሆኗታል።

በእነዚህ የትዳር ቀናት ባል ለሚስቱ ሻዋርማ የተሰኘው ሳንድዊች እንዲገዛላት ብትጠይቅም እስከ የፍቺ ቀን ድረስ አንድም ለመግዛት ፈቃደኛ አልሆነም ነው የተባለው።

በዚህም ጉዳዩ ለዛናኒሪ የቤተሰብ ፍርድ ቤት ያመራችው ሳሜሃ፥ ለጭቅጭቁ መነሻ ባል ለሚስቱ “ሳንድዊች አልገዛም” ማለቱ እንደሆነ አስረድታለች።

ከሁለት ወራት ትውውቅ በኋላ ለአስተማሪው አህመድ የተዳረችው ሳሜሃ፥ የባሏ ባህሪ ከጅማሬው የተገነዘበች አትመስልም።

ከሠርጋቸው በኋላ አህመድ ገንዘብ ያለማውጣት ወይም የጋብሮቭነት ባህሪ እንዳለው ተመልክታለች።

ለዚህም አህመድ በመጀመሪያው የጋብቻቸው ቀን ላይ የገንዘብ ብክነት እንደሚጠላ ለሚስቱ ተናግሮ እንደነበር ተጠቁሟል።

ሳሜሃ በዚያን ጊዜ ለንግግሩ ብዙ ትኩረት ባትሰጥም በትዳራቸው ላይ አንድ ቀን በጨመሩ ቁጥር ነገሮች እየባሱ መሄዳቸው ነው የተነገረው።

ስለሆነም ሳሜሃ ለፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ስታስረዳ ባልና ሚስት ስራ ያላቸው ቢሆኑም፥ አህመድ ምግቡን በሚመገብበት ጊዜም ቢሆን እጅግ ንፉግ እንደሆነ ተናግራለች።

እንደምሳሌ አድርጋ ያቀረበችውም “አህመድ ለስራ ሲወጣ ሁልጊዜ ስንት ዳቦ በቤት እንደነበረ አንድ ሁለት ብሎ ይቆጥራል፤ በዚህም እስከ ቅዳሜና እሁድ ድረስ ሩዝ እና ማኮሮኒ ብቻ እንድበላ ያደርገኛል” ብላለች።

ሳሜህ በመጨረሻ “ከታመመ ባል ጋር መኖር አልችልም” በማለት ትዳሯን አፍርሳ ወደ ወላጆቿ ተመልሳለች ነው የተባለው።

ምንጭ፦ http://www.odditycentral.com/