ሳዑዲ የመዝናኛውን ኢንዱስሪን ለማሳደግ የ64 ቢሊየን ዶላር እቅድ ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ አረቢያ በሚቀጥሉተት 10 ዓመታት የመዝናኛውን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ 64 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እቅድ ይፋ ማድረጓ ተነገረ።

በተያዘው ዓመት ብቻ 5 ሺህ 500 ዝግጂቶች በሀገሪቱ እንደሚዘጋጁ ያስታወቀችው ሳዑዲ፥ እነ ማሮን ፋይቭ እና ሲረል ደ ሶል የሚሳተፍበት የሙዚቃ ዝግጂት እንደሚኖርም አስታውቃለች።

ይህ ውሳኔ የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሳልማን፥ የ2030 የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ መርሃ ግብር አካል መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የኦፔራ ሙዚቃ ቤት ግንባታን አስጀምራለች።

የ32 ዓመቱ ልዑል አልጋ ወራሽ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መሰረት ማስፋት እና ከነዳጅ ጥገኝነት የማላቀቅ እቅድ እንዳለቸው ይነገርላቸዋል።

ሀገሪቱ በታህሳስ ወር በሲኒማ ቤቶች ጥላው የቆየችውን እገዳ ማንሳቷ የመዝናኛውን ኢንዱትሪ ለማሳደግ ቆርጣ መነሳቷን ያሳያል ነው የተባለው።

ሳዑዲ እየወሰደችው ያለው እርምጃ ከዚህ በፊት ከሀገሪቱ ውጭ ይከናውኑ የነበሩትን የተለያዩ የቀረፃ እና የማቀነባበር ስራዎችን ማስቀረት የሚያስችል ነው ተብሏል።

የመዝናኛውን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የላስ ቬጋስ ከተማ መጠን ያለው የመዝናኛ ከተማ ከሪያድ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ለመገንባት ማቀዷኝ ተነግሯል።

ምንጭ ፦ ቢቢሲ