በሰርግ ስነ ስርዓት ለደስታ ተብሎ የተተኮሰ ጥይት የሁለት ሰዎችን ህይወት አጠፋ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሸዋ ዞን በሰርግ ስነስርዓት ላይ ለደስታ ተብሎ የተተኮሰ ጥይት ለሁለት ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ፖሊስ ገለፀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት፥ ጉዳቱ የደረሰው በምስራቅ ሸዋ ሊበን ዝቋላ ወረዳ ሊበን ጋዱላ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ከትናንት በስቲያ በተካሔደው የሰርግ ስነስርዓት ላይ ነው።

በሰርጉ ስነስርዓት ወቅት ለደስታ ተብሎ የተተኮሰ የክላሽ ጥይት አንድ ሰው ይገድላል።

ተኳሹ በስህተት የገደለው የወንድሙን ሚዜ የነበረና በቅርብ የሚያውቀው መሆኑን እንዳረጋገጠ፥ እየሮጠ ከቤት ወጥቶ በዚሁ መሳሪያ እራሱን ማጥፋቱን ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ አስታውቀዋል።

የሁለት ሰዎች ህይወት የጠፋበት የሰርግ ስነስርዓት በተያዘለት መርሃ ግብር መሰረት መከናወኑን ተጠቁሟል።

በደስታም ሆነ በሀዘን ስነ ስርዓቶች ላይ በዘልማድ የሚተኮሱ ጥይቶች የህብረተሰቡን ሰላም የሚያደፈርሱ፣ ህገ ወጥ እና ሌላ መዘዝ ይዘው የሚመጡ በመሆናቸው ከድርጊቱ መታቀብ እንደሚገባም ኮማንደሩ አሳስበዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ