ከ19 ዓመት በፊት የገዙትንና ያልተጠቀሙበትን የአውሮፕላን ትኬት መጠቀም ይችሉ ይሆን?

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካው ዩናይትድ አየር መንገድ አንድ ደንብኛ ከ19 ዓመት በፊት የገዛው እና ያልተጠቀመበት የአውሮፕላን ትኬት ዛሬ ዋጋ አሰጥቶታል።

ጆን ዋኬር የተሰኘው አሜሪካዊ ግለሰብ ትኬቱን የገዛው በአውሮፓውያኑ ታህሳስ ወር 1998 ሲሆን፥ ከናሽቪሌ ወደ ሳክራሜንቶ ግዛት ለመብረር ነበር።

ይህም የጉዞው ምክንያት በጥር ወር 1999 በሚደረገው የሚስቱ ወንድም ሰርግ ለመገኘት እንደነበር ነው የተናገረው።

ይሁን እንጂ “በተባለው ቀን አልሄድኩም” ያለው ዋኬር፥ በወቅቱ ተመላሽ ገንዘብ እንዲሰጠው ጠይቆ እንደነበር ነው የገለፀው።

በዚህም የሀገሪቱ አየር መንገድ በመጋቢት 1999 በላከው ደብዳቤ መሰረት፥ “የትኬቱ ዋጋ ተመላሽ ባይደረግለትም ለወደፊቱ በረራ ግን ሊውል ይችላል፤” ሲል መልስ እንደሰጠው ተነግሯል።

ዌከር በዚያን ወቅት ለመጓዝ ዕቅድ ስላልነበረው ትኬቱን ቤቱ ውስጥ ቢያስቀምጠውም ከዚያ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ረስቶታል።

ዌከር አንድ ቀን ከአልጋው ስር ሌላ ነገር ሲፈልግ በአጋጣሚ ከ19 አመት በፊት የቆረጠውን የአየር ቲኬት አገኘ፤ በኋላ ሳጥኑን ሲከፍትም ከአየር መንገዱ የተፃፈለት ደብዳቤን ማግኘቱን ነው የተናገረው።

በዚህም ትኬቱን ለመጠቀም የሚያስችለውን ፈቃድ ለማግኘት የአየር መንገዱ የደንበኛ አገልግሎት ክፍል በተደጋጋሚ ቢጠይቅም፥ ትኬቱ ጥቅም ላይ ሳይውል ለረጅም ጊዜ የተቀመጠ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ማንም ሰራተኛ በዚህ ትኬት ምን እንደሚሰራ አያውቅም ነበር ነው የተባለው። 

ይሁን እንጂ ዌከር በዚህ ሁኔታ ተስፋ ሳይቆርጥ በትዊተር አማካኝነት ለድርጅቱ መልእክት ለመላክ መወሰኑን ተገልጿል።

ታድያ ከተደጋጋሚ ጥረት በኋላ ግለሰቡ ያሰበው ተሳክቶለት አየር መንገዱ ጥያቄውን ተቀብሎታል።

በዚህም ዌከር በ378 የአሜሪካ ዶላር የገዛው ትኬት በአሁኑ ሰአት ባለው የ571 ነጥብ 6 ዶላር ሂሳብ መሰረት ያለ ተጨማሪ ክፍያ እንዲስተናገድ እየጠበቀ መሆኑን ተነግሯል።

boarding-pass.jpg

 

 

ምንጭ፦www.independent.co.uk