ከመሬት 900 ሜትር ከፍታ በታሰረ ቀጭን ገመድ ላይ የተራመደው ወጣት የበርካቶችን ቀልብ ስቧል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) ከመሬት 900 ሜትር ከፍታ ላይ በታሰረ ቀጭን ገመድ ላይ የተራመደው ወጣት የበርካቶች የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።

ወጣቱ በአውሮፓውያኑ 2017 “ኢንተርናሽናል ሀይላይን ቻለንጅ” በተባለ በደቡብ ምዕራብ የቻይና ዩናን ግዛት በዲሊ ከተማ ውስጥ በሺመንጉዋን ጂኦፓርክ ባደረገው የገመድ ላይ መራመድ አስደናቂ ውድድር የዓለም የድንቃድንቅ ክብረወሰንን ይዟል።

ስላክሊንግ አንድ ወይም ሁለት ኢንች ስፋት ባለው እና ከመሬት ከፍ ብሎ በሚታሰር ቀጭን ገመድ ሚዛንን ጠብቆ የሚደረግ ስፖርታዊ ውደድር መጠርያ ነው።

ይህ የስፖርት ዓይነት ከመሬት በላይ እስከ 900 ሜትር ባለው ከፍታ በተዘረጋ ገመድ ላይ የሚደረግ ሚዛንን ጠብቆ የመራመድ ውድድር ሲሆን፥ በዚህ የከፍታ ገደል በእግር መራመድ “አጉል ደፋር ሰው” ያሰኛል ነው የተባለው። 

በዚህ ፌስቲቫል ሶስት አትሌቶች ስማቸው በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ለማስፈር ሲሉ ስላክሊንግ በተሰኘው ውደድር ረጅሙን የእግር ጉዞ ለማድረግ ሙከራ አድርገዋል።

በዚህም ፓብሎ ሲግኖሬት የተባለው ተወዳዳሪ ዙሩን በ25 ደቂቃ በገመድ ላይ ተጉዞ በማጠናቀቁ አዲሱን ክብረ ወሰን በእጁ ማስገባቱ ተነግሯል። 

የዓለም አቀፍ የስላኪንግ ዴቨሎፕመንት ድርጅት ፕሬዚዳንት የሆኑት አንቶኒ ኒውተን እንዳረጋገጡት፥ ስፖርቱ ክብረ ወሰኑን ከመያዝ ባሻገር ሲታይ በደህንነት ጉዳዩ ስጋቶች ያሉት ነው።

በዚህም ብዙ አስተያየት ሰጪዎች ከውድድሩ በኋላ በሰጡት አስተያየት ተወዳዳሪዎቹን የተለዩና ሰው ሊያደርገው የማይደፍረውን የሚያደርጉ በሚል ሲገልጿቸው፥ ውድድሩን ደግሞ አደገኛ ብለውታል።

ይሁን እንጂ ተወዳዳሪዎቹ ለወደፊቱ ከዚህ የተሻለ አዲስ ከብረ ወሰን ለመስበር እንደሚፈልጉ ነው የተነገረው።

848203b7-10ad-437c-8449-0596b99e01a1.jpg

ምንጭ፦ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን.