የቻይና ካሊግራፊ ስዕሎች በ144 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ተሸጡ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናዊው ሰዓሊ ኩይ ባኢሺ ተፈጥራዊ አካባቢዎችን የሚያሳዩ 12 የካሊግራፊ ስዕሎች በ144 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ በጨረታ ተሸጡ።

የስዕሎቹ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቻይና የስዕል ጥበብ ከዚህ ቀደም የተሸጠበትን የጨረታ ዋጋ ክብረ ወሰን አሻሽሏል።

ሰዓሊ ኩይ ባለ 12 ፍሬም የተፈጥሮ አካባቢዎችን የሚያሳየውን አዲስ ጥበብ የፈጠረው በፈረንጆቹ 1925 ነው።

በዚህ የአሳሳል ጥበብ የስዕሎቹ ቁመት 1 ነጥብ 8 ሜትር ርዝመት ይኖረዋል።

ሰዓሊው ይህን የአሳሳል ዘዴ ለመተግበር የተነሳሳው በሀገሪቱ ባደረጋቸው ጉዞዎች ባየው የተፈጥሮ ውበት በመሳቡ ነው።

ስዕሉን በአንድ ወቅት በቤጂንግ ታዋቂ ሃኪም ለነበረው ጓደኛው ቼን ዚሊን ይሰጠዋል፤ ጓደኛው ዶክተር ዚሊን ስዕሎቹን ትናንት በቤጂንግ ለጨረታ ያቀረባቸው ሲሆን፥ የመነሻ ዋጋቸውም 450 ሚሊየን የቻይና ዩዋን ነው።

ከ57 የጨረታ ዙሮች በኋላም አንድ ገዥ በስልክ ደውሎ 810 ሚሊየን ዩዋን እገዛቸዋለሁ አለ።

በመጨረሻም ሌላ ሰው ስዕሉን በ931 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩዋን ወይም በ144 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ለመግዛት በመስማማት አሸንፏል።

በዚህም ሰዓሊ ኩይ ከ100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የተሸጠ የቻይና ስዕል ባለቤት በሚል የመጀመሪያው ሆኗል።

ምንጭ፦ሲ ጅ ቲ ኤን