ለ18 ዓመታት የመኪና ጡሩምባ ሳያሰማ ያሽከረከረው ህንዳዊ ተሸልሟል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ18 ዓመታት የመኪና ጡሩምባ (ክላክስ) ሳያሰማ ያሽከረከረው ህንዳዊ የአካባቢ የድምፅ ብክለት እንዳይከሰት ያደረገ በሚል ተሸልሟል።

ግለሰቡ “ማኑሽ ሳንማን” የተባለ ሽልማት የተበረከተለት መሆኑም ተነግሯል።

እንዲህ አይነት ሽልማት ለበርካቶች ግራ ሊያጋባ የሚችል እና ያልተለመደ ቢሆንም፥ ህንድ ግን በመኪና ጡሩምባ/ክላክስ አማካኝነት ከፍተኛ የሆነ የድምፅ ብክለት ያጋጥማታል።

አብዛኛው የህንድ አሽከርካሪዎችም የመኪና ጡሩምባ አዘውትረው በመጠቀም ነው የሚታወቁት።

ዲፓክ ዳስ የተባለው የህንድ ኮልካታ ነዋሪ፥ ህንድ ይህንን መቀየር እንደምትችል እና ሰላማዊ እና ፀጥታው የተከበረ መንገዶች እንደሚኖራት እምነት አለኝ ብሏል።

ህንድ ውስጥ መኪና የሚያሽከረክሩ ሰዎች ዘንድ የመኪና ጡሩንባ መንፋት የተለመደ ሲሆን፥ አንዳንዶች እንደ ጎን መስታወት ይጠቀሙታል ነው የሚባለው።

የጎን መመልቻ መስታወት እያላቸው እንኳ፤ የተወሰኑት የጎን መስታወት ስለሌላቸው ግጭት ሊፈጠር ይችላል።

ይህን ለማስቀረትም የህንድ አሽከርካሪዎች በብዛት የመኪና ጠሩንባ መጠቀምን ይመርጣሉ፤ አሽከርካሪዎቹ ለማለፍ ሲፈልጉ እና ሌላ ተሽከርካሪዎች እንደቀረባቸው ለመግለፅም የመኪና ጡሩምባ አብዝተው ይጠቀማሉ።

ይህ ደግሞ የአካባቢ ድምጽ ብክለትን እያስከተለ ነው የተባለው።

ለበርካታ የህንድ ታዋቂ ሰዎች በሹፌርነት የሰራው ዲፓክ ዳስ የተባለው ህንዳዊ ግን ከእነዚህ አሽከርካሪዎች አይመደብም የተባለ ሲሆን፥ የድምጽ ብክለትን ላለማስከተል የሚያደርገው ጥረትም ከበርካቶች አድናቆትን አትርፎለታል።

የማኑሽ ሜና ሽልማት አዘጋጆችም ዲፓክ ዳስ የማሽከርከር ልምድን ካጣሩ በኋላ “ማኑሽ ሳንማን” የሚባለው ሽልማት እንዲበረከትለት መርጠውታል።

የማኑሽ ሜና የተባለው የሽልማት ተቋም በሀገሪቱ ውስጥ ለየት ያለ ተግባር የሚያከናውኑ ሰዎችን እየለየ ነው የሚሸልመው።

ምንጭ፦ www.odditycentral.com