በዳ ቪንቺ የተሰራው የእየሱስ ክርስቶስ ምስል በ450 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተሸጧል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ ስራ የሆነውና 500 አመት እድሜ እንዳለው የሚነገርለት የእየሱስ ክርስቶስ ምስል በከፍተኛ ገንዘብ ወደ አቡ ዳቢ አምርቷል።

የአለም አዳኝ የሚል መጠሪያ ያለው ይህ የእየሱስ ክርስቶስ ምሰል አዲስ ወደተከፈተው ሎቭሬ ሙዚየም ማቅናቱም ነው የተነገረው።

ከተከፈተ ወር ያልደፈነው የአቡ ዳቢው ሎቭሬ ሙዚየም 10 አመታትን ለግንባታ የፈጀ ሲሆን፥ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ደግሞ ወጪ ተደርጎበታል።

ሙዚየሙ ከተለያዩ የአለም ክፍሎች ከሚገኙ አቻዎቹ የተለያዩ የስነ ጥበብ ስራዎች እየሰበሰበ ሲሆን፥ አሁን ላይ 600 ስራዎችን በቋሚነት ይዞ ይገኛል።

ከዚህ ባለፈም 300 የስነ ጥበብ ውጤቶችን ከፈረንሳይ በተውሶ አስመጥቷል።

ሙዚየሙ መጠሪያ ስሙን ከፈረንሳይ የተዋሰው ሲሆን፥ ለዚህም ምስጋናውን አቅርቧል።

በሳዑዲው ልዑል ሳይገዛ እንዳልቀረ የተነገረለት የዳ ቪንቺ ስራ 450 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታልም ነው የተባለው።

በፈረንጆቹ 15 05 እንደተሰራ የሚነገርለት ይህ የጥበብ ስራ በጥሩ ይዞታ ላይ ሆነው ዘመን ከተሻገሩ የሰዓሊው ድንቅ ስራዎች አንዱ መሆኑ ይነገራል።

ጣሊያናዊው ዳ ቪንቺ በ15 19 በፈረንሳይ ህይዎቱ ያለፈ ሲሆን፥ በህይዎት ዘመኑ ከሰራቸው ድንቅ የስነ ጥበብ ስራዎቹ መካከል ከ20 የማይበልጡት ብቻ በግለሰቦች እጅ ይገኛሉ።

ሞናሊዛ፣ የመጨረሻው እራት፣ በመላዕክት የምስራችን የገለጸበት የማብሰር ስዕሉ እንዲሁም ጦርነትን፣ ተፈጥሮን፣ የሰውን ልጅ አኗኗርና ተፈጥሮን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የሰራቸው የስነ ጥበብ ዘመን ታሻጋሪ ስራዎቹ ዳ ቪንቺን ዛሬም ድረስ ታላቁ ሰዓሊ ያደርጉታል።

ዛሬም ድረስ ሁሉንም የሚያስማማ ትርጉም ያልተሰጣት ሞናሊዛ ደግሞ የዳ ቪንቺ የምንጊዜም ድንቅ ስራው እንደሆነች ይነገራል።

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ