ሃኪሞች ከአንዲት ሴት ጨጓራ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የፀጉር ጥቅል አስወገዱ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህንድ ሃኪሞች ከአንዲት ሴት ጨጓራ ውስጥ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የፀጉር ጥቅል ቀዶ ህክምና አስወግደዋል።

ማሃራጃ የሽዋንትራ የመንግስት ሆስፒታል ሶስት ሰዓታትን በወሰደው ቀዶ ህክምና ከ25 ዓመቷ ህንዳዊት ወጣት ጨጓራ ውስጥ ጥቅል ፀጉሩ ወጥቶላታል።

ዶክተር አር ኬ ማቱር አምስት ሃኪሞችን የያዘው የቀዶ ህክምና ቡድን መሪ ሲሆኑ፥ አሁን ወጣቷ በመልካም ጤንነት ላይ ናት ብለዋል።

ወጣቷ የአዕምሯዊ ቀውስ ተጠቂ ስትሆን፥ ይህም የራሷን ፀጉር እንድትመገብ እና እየበጣጠሰች እንድትመገበው ያደርጋት እንደነበር ነው የተገለፀው።

በዚህም ከበርካታ ጊዜ በኋላ ወደ ሆዷ የገባው ፀጉር በጨጓራዋ ተከማችቶ ትልቅ እብጠት መፍጠሩ ተነግሯል።

ፀጉሯ ከጨጓራዋ ባይወገድ ኑሮ የአዕምሮ ህመም ተጠቂዋ ወጣት ጤንነት በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይደርስ ነበር ብለዋል ዶክተር ማቱር።

ምንጭ፦ ndtv.com