በተገቢው መንገድ አላስተማረኝም ያለው ግለሰብ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲን የ1 ሚሊየን ፓውንድ ካሳ ጠይቋል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በተገቢው መንገድ ስላላስተማረኝ የምፈልገውን ስራ እንዳላገኝ አድርጎኛል ያለው ግለሰብ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲን 1 ሚሊየን ፓውንድ ካሳ ጠይቋል።

ዩኒቨርሲቲውን የከሰሰው ተመራቂ ፋይዝ ሲዲቁ ይባላል፤ በትምህርት ጥሩ ውጤት አምጥቶ የተዋጣለት የህግ ጠበቃ መሆንም ዓላማው ነበር፤
ሆኖም ማምጣት ያለበትን የ2፡1 የዲግሪ ውጤት ሳያስመገዘብ ቀርቷል።

ይህን ተከትሎም ፋይዝ ሲዲቁ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ብቁ እንድሆን አድርጎ አላስተማረኝም በሚል ዩኒቨርሲቲውን በፍርድ ቤት ከሶታል።

ሲዲቁ “ዩኒቨርሲቲው በተገቢው መንገድ ስላላስተማረኝ በምወደው ሙያ ተሰማርቼ የመስራት እድልን አጥቻለሁ፤ በመሆኑም ለፈፀመብኝ በደል 1 ሚሊየን ፓውንድ ካሳ ሊከፍለኝ ይግባል” የሚል ክስ አቅርቧል።

“ኦክስፎርድ በተገቢው መንገድ ቢያስተምረኝ ኖሮ የብቃት ፈተናውን አልፌ የኩባንያዎች የህግ ጠበቃ እሆን ነበር፤ ነገር ግን በዩኒቨርሲቲው ስህተት ያ ሊሆን አልቻለም” ይላል ፋይዝ ሲዲቁ።

በተለይም በዘመናዊ ታሪክ ትምህርት ማሟያ በተገቢው መንገድ ስላልተማርን በፈረንጆቹ 2000 ሰኔ ወር ላይ የተሰጠንን የማጠቃለያ ፈተና ማለፍ አልቻልኩም ብሏል።

የተወሰኑ መምህራን በትምህርት ክፍለ ጊዜ እንደማይገቡ እና የማካካሻ ትምህርት አለመሰጠቱም በውጤቱ ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠሩን ነው ያነሳው።

ሲዲቁ ዝቅተኛ ውጤት በማምጣቱ ለከፋ የእንቅልፍ እጦት እና የአዕምሮ ድብርት መዳረጉን ተናግሯል።

ጠበቃው ሮበርት ማላሊዩ የደንበኛዬ 2:1 የማጠቃለያ ውጤት አለማምጣት፥ ተስፈኛውን ወጣት የማይመጥን እና በዩኒቨርሲቲው ግዴለሽነት የመጣ በመሆኑ ፍርድ ሊሰጥ ይግባል የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።

በተለይም ሲዲቁ ታሞ በነበረበት ወቅት ያለፉትን ትምህርቶች አለመማሩና በዩኒቨርሲቲው የግል አስተማሪው መታመሙን ባለማሳወቁ የፈተና ጊዜ ፈቃድ እንዳያገኝ አድርጎታል፤ ይህ ደግሞ ዝቅተኛ ውጤት ለማምጣት ምክንያት ሆኗል የሚል ክስ አቅርቧል ጠበቃው።

በአሁኑ ወቅትም ሲዲቁ ስራ አጥ ነው፤ ይህ ደግም ጉዳቱን የከፋ ያደርገዋል ብሏል በክሱ የቀረበው ዝርዝር።

ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ የቀረበው ውንጀላ ሀሰት ነው ያለ ሲሆን፥ የክስ ጉዳይም በህግ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ያለፈ በመሆኑ እንድማይቀበለው ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱም በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት የሰባት ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል ነው የተባለው።

ምንጭ፦ኢንዲፔንደንት