መንገድ ዳር ሲሸኑ የታዩት የህንዱ ሚኒስትር ወቀሳ ቀርቦባቸዋል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህንድ መንግስት ሰዎች መፀዳጃ ቤት መጠቀምን ባህል እንዲያደርጉ በዘመቻ መልክ በመስራት ላይ ባለበት ወቅት መንገድ ዳር ሲሸኑ የታዩት የመንግስት ሚኒስትር ወቀሳ ቀርቦባቸዋል።

ራም ሻዲን የተባሉት ሚኒስትር መሃራሽታራ በተባ ስፍራ ላይ ሲሸኑ የሚያሳየው ቪዲዮም እሁድ በተከበረው የዓለም የመፀዳጃ ቀን በኢንተርኔት ላይ የተለቀቀ ሲሆን፥ ቪዲዮውንም በሺህ የሚቆጠሩ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች ተጋርተውታል።

ይህንን ቪዲዮ ያገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይህ ተግባር ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በጽዳት ላይ የጀመሩት ዘመቻ መክሸፉን ያሳያል እያሉ ነው።

ሚኒስትሩ በበኩላቸው፥ “ተፈጥሮ ላቀረበችልኝ ጥሪ ነው ምለላሽ የሰጠሁት፤ በወቅቱ ጥሩ ስሜት አልተሰማኝም ነበር፤ በአካባቢው ደግሞ መፀዳጃ ቤት ማግኘት ባለመቻሌ እንዲህ ለማድረግ ተገድጃለው” ብለዋል።

የውሃ ሚኒስትር ደኤታ የሆኑት ራም ሻዲን፥ በመስኖ ልማት ዙሪያ የተሰሩ ስራዎችን ለመመልከት ጉዞ በማድረግ ላይ እያሉ በደቡብ ምእራብ መሃራሽታራ ቢሳሪ እና ሶላፑት በተባሉ ስፍራዎች መካካል ባለ መንገድ ላይ መሽናታቸውንም ተናግረዋል።

“ሞቃታማ አየር ውስጥ ረጅም ርቀት ያለ እረፍት መጓዝ እና የአካባቢው አቧራማነት እንድታመም አደረገኝ፤ በወቅቱም ከፍተኛ ተኩሳት ነበረኝ” ብለዋል።

ሆኖም ግን ተቃዋሚው ናሽናሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሚኒስትሩ በመንገድ ላይ እያሉ የሚፀዳዱበትን ስፍራ ማጣታቸው መንግስት የህዝብ መፀዳጃዎችን እሰራለው ብሎ የያዘው እቅድ አለመሳካቱን ያሳያል እያለ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እንዲህ አይነት ተግባር የሚፈፅሙ ሚኒስትሮችን ይዘው እንዴት ህዝቡ ስነ ምግባር እንዲይዝ ይጠብቃሉ ብሏል ፓርቲው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ህንድን ማፅዳት የሚለውን ዘመቻቸውን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ነበር የተጀመረው።

በዚህ ዘመቻም መንግስት በመላው ሀገሪቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ መፀዳጃ ቤቶችን እንደሚገነባም ቃል ገብተዋል።

ምንጭ፦ www.bbc.com