ባልፈፀመው ወንጀል ለ46 ዓመታት ታስሮ የኖረው ግለሰብ በመጨረሻም ተፈቷል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ባልፈፀመው የማገት እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል ለ46 ዓመታት ታስሮ የኖረው አሜሪካዊው ዊልበርት ጆንስ የተባለ ግለሰብ በመጨረሻም ተፈቷል።

ከትናንት በስቲያ ከእስር ሲወጣ ስለወደፊት ህይወቱ እቅዱን ተናግሯል።

ዊልበርት ጆንስ ይባላል፤ በአሜሪካ ሉዚያና ግዛት ነዋሪ ነበር፤ አሁን የ65 ዓመት አዛውንት ነው።

ዊልበርት ጆንስ የግዛቱ ፍርድ ቤት ከ2 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲሰጠውና ከእስር ነፃ እንዲሆን በወሰነው መሰረት ከእስር ቤት ሲወጣ ምንም ዓይነት የተለየ ስሜት እንዳልነበረው ተገልጿል።

ጆንስ ከማረሚያ ቤት ሲወጣ ቤተሰቦቹ ከችሎት አዳራሽ ውጭ በእንባ እየተራጩ ተቀብለውታል።

“አሁን ላይ ጥሩ የድንች ሳላድና ጣፋጭ ምግቦችን እፈልጋለሁ ያለው ጆንስ፤ ቀሪዋን ውስን ህይወቴን በደስታ ማሳለፍ እፈልጋለሁ፤ ህፃናትም በትክክልኛ መንገድ እንዲሄዱ አስተምሯቸዋለው” ነው ያለው።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፥ ጆንስ በፈረንጆቹ 1971 አንዲትን ነርስ በአሜሪካ ሉዚያና ግዛት ባቶን ሮጅ ሆስፒታል የመኪና ማቆሚያ ስፍራ በማገት አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተጠርጥሮ ተያዘ።

በፈረንጆቹ ጥቅምት 2 ቀን 1971 ከህንፃ ጀርባ በመሰወር ማገትና አስገድዶ መድፈር ወንጀሉ ሲፈፀም ዊልበርት የ19 ዓመት ወጣት ነበር።

በፈረንጆቹ 2008 ህይወቷ ያለፈው ነርሷ ጆንስ እንዲታሰር ብቸኛ የወንጀሉ ማስረጃ እና ምስክር ነበረች።

ይኸውም ጆንስ እና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ነርሷ ከተደፈረች ከሶስት ወር በኋላ እንዲሰለፉ ተደርጎ ወንጀለኛው ማን ነው የሚለውን መረጠች።

ጆንስ ከሌሎቹ አንፃር አጭር እና የተለየ ድምፅ የነበረው ሲሆን፥ ተጎጂዋ ነርስ ደፈረኝ ብላ ያቀረበችው ወንጀለኛ ግን ረጅም እና ድምፀ ሸካራ ነበር ተብሏል።

በ1974 እንደገና በታየው የወንጀል ችሎትም ባልፈፀመው ወንጀል ነርሷ ባቀረበችው የማያስተማምን ማስረጃ መሰረት በጥርጣሬ ብቻ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

የጆንስ ጠበቃ አንደርሰን ነርሷ ያቀረበችው የግለሰቡን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልፅፀው ማስረጃ ነርሷ ከተደፈረች ከ27 ቀናት በኋላ ሌላ ሴት በመድፈር ተጠርጠሮ የነበረ ግለሰብ ጋር የተመሳሰለ ነው የሚል መቃወሚያ አቅርቧል።

ነርሷ ከሰጠችው መረጃ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አንድ ግለሰብ በ1973 ሌላ ሴት በመድፈር ተጠርጥሮ ቢያዝም፥ እስር የተላለፈበት ግን በጦር መሳሪያ አስፈራርቶ በመዝረፍ ወንጀል ነው ተብሏል።

ጠበቃ አንደርሰን ፖሊስ ተጎጂዋ የሰጠችውን አካላዊ ማስረጃዎች ከማን ጋር እንደሚመሳሰል በእርግጠኛነት እንደሚያውቅ መረጃዎች ያሳያሉ ብለዋል።

አሁን ላይ 46 ዓመታትን በእስር ያሳለፈው ጆንስ የተፈታ ሲሆን፥ 2 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ካሳም ይገባዋል ተብሏል።

ነፃ እንዲሆን ዓመታትን ወንጀሉ እንደገና እንዲጣራ ሲደክሙ ከኖሩት ቤተሰቦቹ ጋርም ተገናኝቷል።

“የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ጆንስ ድርጊቱን እችንዳልፈፀመ እናውቅ ነበር፤ ነፃ መሆን እንዳለበት እና ይህም አንድ ቀን እንደሚሆን ተስፋ ነበረኝ ሲል ወንድሙ ፔልም ጆንስ ተናግሯል።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ብናከብርም በምን ያህል ሀቀኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ውሳኔ እንድሰጠ ለማረጋገጥ ይግባኝ መጠየቃችን አይቀርም ነው ያለው አቃቤ ህጉ።

በጆንስ የቀረበው የወንጀል ማስረጃ በጣም ደካማ ቢሆንም በጥርጣሬ ታስሮ መኖሩን አልደበቀም።

የጆንስ እጮኛ ዋጄዳ ጆንስ በአሜሪካ ሉዚያና ግዛት የታዋቂ የሆነውን ጉምቦ እና የድንች ሳላድ ምግብ እናዘጋጅለታለን ነው ያለችው።

ከሳሽ አቃቤያን ህግ የሉዚያና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እንደገና እንዲመለከተው ይግባኝ እንደሚጠይቁ ገልፀው፥ ነገር ግን ጆንስ ድጋሜ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ አናደርግም ነው ብለዋል።

የማርሚያ ቤቱ አስተባባሪ ቲሞቲ ሁፐር ጆንስ ወደ ማረሚያ ቤቱ ከገባ ጀምሮ በውስጡ የሚገኘውቅ ማህበረሰብ ተለውጧል፥ እሱ ለሌሎች ሰዎች መልካም አርዓያ ነው፥ ወንጀል ሰርቷል የሚል ግምት የለኝ ሊፈታ ይግባል የሚል የምስክርነት ቃል መስጠቱም ተገልጿል።

ምንጭ፦ኢንዲፔንደንት