459 የጭማቂ መምጠጫዎችን በአፉ በመክተት በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ የሰፈረው ህንዳዊ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 459 የጭማቂ መምጠጫዎችን በአፉ በመክተት በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ የሰፈረው ህንዳዊ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

ህንዳዊው ማኖጅ ኩማር ማሃራና በዚህ ተግባሩ ላለፉት ስምንት ዓመታት ማንም ያላሻሻለውን የዓለም ክብረ ወሰን ሰብሯል።

በሀገሪቱ ኦዲሻ አካባቢ የሚኖረው ይህ የ23 ዓመት ወጣት በአፉ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የጭማቂ መምጠጫዎችን በማስገባት የድንቃ ድንቅ ውድድር ተሳትፎ ነው ይህን ድል ያገኘው።

በዚህም 459 የተለያዩ ቀለማት ያላቸውና ዝቅተኛ መጠነ ዙሪያቸው 0 ነጥብ 69 ሳንቲ ሜትር የሆኑ መምጠጫዎችን በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በአፉ መክተት ችሏል።

የድንቃድንቅ ክብረ ወሰኑን ለማሻሻልም ከቁጥራቸው ባሻገር መምጠጫዎችን በአፉ ይዞ ቢያንስ ለ10 ሰከንዶች ያለምንም እንከን መቆየት ነበረበት።

የድንቃድንቅ ሁነት ውድድሮች ህግ በዚህ ፉክክር ሂደት በ10 ሰከንድ ቆይታቸው መምጠጫዎቹን በእጃቸው መያዝ አይፈቀድላቸውም።

ማኖጅ ከልጅነቱ ጀምሮ የዓለም ድንቃ ድንቅ ክብረ ወሰብን የመቀዳጀት ፍላጎት የነበረው ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ሲሞን ኤልሞር በተባለ ግለሰብ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሽሏል።

ብሪታኒያዊው ሲሞን ኤልሞር ከዚህ ቀደም በአፉ መክተት የቻለው 400 የጭማቂ መምጠጫዎችን ነበር።

ምንጭ፦ www.guinnessworldrecords.com