ባለቤቴ ቤት ውስጥ ምንም እንዳልሰራ ከለከለኝ ያለችው ግብፃዊት በተጋቡ በ2ኛ ሳምንት ፍቺ ጠይቃለች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግብፃዊቷ ሴት ባሏ ሙሉ የቤት ስራዎችን እየሰራ በመሆኑ በተጋቡ በሁለት ሳምንት ውስጥ የፍቺ ጥያቄ አቅርባለች።

የ28 ዓመቷ ግብፃዊት አዲስ መሽራ ሰማር ትባላለች፤ ከባሏ ጋር ትዳር መስርተው ያለፉትን ሁለት ሳምንት አብረው ናቸው።

ሆኖም ባሏ ሙሉ የቤት ውስጥ ስራዎችን ማከናወኑ ሚስትን አላስደሰተም።

የ31 ዓመቱ ባል ሞሃመድ ይባላል፤ የልብስ መደብር ቢኖረውም ሙሉ ሰራተኞችን በመቅጠር እሱ ጊዜውን የሚያሳልፈው በመኖሪያ ቤት ውስጥ ከሚስቱ ጋር ነው።

ሚስት ባሏ ሙሉ ጊዜውን ቤት ሲያፀዳ ሲያደራጅ እና ሌሎችን ስራዎችን ሲሰራ መዋሉ ከእርሱ ጋር በትዳር እንዳልቀጥል አድርጎኛል ትላለች።

“ባሌ ነገረ ስራው ሁሉ ልክ እንደ ቤት እመቤት ነው፤ ይህ ደግሞ ስለእሱ እንድጨነቅ እያደረገኝ ነው፤ የቤት ውስጥ ስራዎችን በሙሉ ማከናወን ብቻ ሳይሆን ላግዝህ ስለው እንኳ አይፈቅድልኝም” ትላለች ሰማር።

ሚስት እባክህ እኔም መስራት አለብኝ ብላ ብትሞግትም፥ ባል ግን አብረን እንድንቀጥል ከፈለግሽ የእኔን ደንቦች ልታከብሪ ይግባል በሚል የቤት ውስጥ ተቀማጭ አድርጓታል።

“ከተጋባን ሁለት ሳምንታችን ነው፤ ለሁለት ዓመታት ያህል በፍቅር ስለቆየን በጣም አውቀዋለሁ እወደዋለሁ፤ ሆኖም ከተጋባን በኋላ የሚያደርጋቸው ተግባራት ሁሉ እንድጠላው እና እንድፈታው አስገድዶኛል” ብላለች።

“ባለቤቴ የቤት እመቤት ነው፤ በቤታችን ውስጥ ምንም ዓይነት ነገር እንዳልሰራ ይከለክልኛል፤ ወጥ የሚሰራው፣ ቤት የሚያፀዳው፣ እቃዎችን የሚያደራጀው እና ሙሉ የቤት ስራዎችን የሚሰራው እሱ ነው፤” ስትል ተናግራለች።

“በቤት ውስጥ ሁሉንም ነገር ይቆጣጠራል፤ ቴሌቪዥን ጣቢያ እሱ ካደረገው ውጭ መቀየር አልችልም፤ የራሱ የንግድ ስራ ቢኖረውም ሰራተኞች ቀጥሮ እሱ ውሎውን በቤት ውስጥ አድርጓል፤ ይህም እንድፈታው አስግድዶኛል” ስትል ነው አቤቱታ ያቀረበችው።

ሰማር ለባሏ እናት ስለ ሞሃመድ ተግባራት ስትነግራቸው፥ እናቱ “ይህ ልጅ ይህን ባህሪ ከየት አመጣው? ከዚህ ቀደም አድርጎት አያውቅም ነበር እኮ” በሚል ተገርመዋል።

በቤት ውስጥ ልብስ የሚያጥበው፣ ምግብ በማቀዝቀዣ ውስጥ የሚያስቀምጠው እና አልጋ የሚያስተካክለው እሱ በመሆኑ ኑሮየን አሰልቺ ስላደረገው መፍታት ግድ ሆናል ነው ያለችው።

“ባሌ ነፃነቴን እየሰጠኝ አይደለም፤ በቤት ውስጥ ጉዳዮች ሙሉ አዛዥ እሱ ነው፤ በቤት ውስጥ ባለቤትነት አይሰማኝም፤ ለጋብቻ የተሰጠኝን ስጦታ በመመለስ መፍታት እፈልጋለሁ” የሚል የፍች ጥያቄ ለግብፅ የቤተሰብ ፍርድ ቤት አቅርባለች።

በፍች ጥያቄው ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል