አርጀንቲናዊው ወጣት ለጡረታ ውርስ ሲል የ91 ዓመቷን የወላጁን አክስት አግብቷል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ ሰዎች የስጋ ዘመዳቸውን እስከማግባት እንደሚደርሱ ከአርጀንቲና የተገኘው ዜና ይነግረናል።

አርጀንቲናዊው ወጣት ከሞት በኋላ ለዘመድ የሚሰጥን የጡረታ ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲል የ91 ዓመት እድሜ ባለ ፀጋ ከሆኑት የወላጁ አክስት ጋር ትዳር መመስረቱ ተሰማምቷል።

ከወላጁ አክስት ጋር የሚኖረው የ25 ዓመት አርጀንቲናዊው ወጣት ማሪሲዮ ኦሳላ፥ በገንዘብ እጥረት ምክንያት የህግ ትምህርቱን ለማቋረጥ እንደሚገደድ ለእኝህ የወላጆቹ አክስት ለሆኑት ሴት ይናገራል።

የወላጁ አክስት የሆኑት የ91 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ሴት ወጣቱ ትምህርቱን እንዳያቋርጥ የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተውለት ነበር።

በመጨረሻም አዛውንቷ ከህልፈታቸው በኋላ የጡረታ ክፍያቸውን ወጣቱ መውሰድ ይችል ዘንድ የስጋ ዘመዳቸው የሆነውን እና በእድሜ የሚራራቁትን ወጣት አግብተዋል።

አርጀንቲናዊው ወጣት የጋብቻ ጥያቄውን ለወላጁ አክስት ያቀረበው እሱ መሆኑን ተናግሯል ።

ምንጭ፦ odditycentral.com