በሃገራት ለህፃናት በመጠሪያነት የማያገለግሉ ስሞች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዓለም ላይ በሚገኙ ሀገራት በርካታ ስሞች ለህፃናት እንዳይወጡ ተከልክለዋል።

ከዚህ ቀደም ሳዑዲ ዓረቢያ የከለከለቻቸውን እንደ አሊስ፣ ማያ እና አብዱል ናስር ያሉ ስሞችን በሀገር ውስጥ ሚኒስቴር አማካኝነት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል።

ገልፍ ኒውስ የተባለው የዱባይ ጋዜጣ አብዱል ናስር የተባለው ስም በሳዑዲ ዓረቢያ ለልጆች እንዳይወጣ የተከለከለው የግብፅ የቀዝቃዛው ጦርነት ብሔራዊ መሪ ገማል አብደል ናስር ጋር በተያያዘ መሆኑን ይጠቅሳል።

ከዚህ ውጭ የተከለከሉ ስሞችን ለመጥቀስ ያህል፦

ቫይኪንግ፣ ጂሚ፣ ሪሃና እ ነና ሳዮናራ - በፖርቹጋል

አሊስ፣ ማያ እና አብዱል ናስር - በሳዑዲ ዓረቢያ

በአንድንድ ሀገራት ደግሞ ፆታ የማያሳውቁ ስሞች የሚከለከሉ ሲሆን ጀርመን እና ዴንማርክ በዚህ በኩል ይጠቀሳሉ።

ዴንማርክ ወላጆች ለህፃናት ስም እንዲያወጡ 7 ሺህ ስሞችን ይፋ ያደረገች ሲሆን ከዚህ ውጭ የሚወጣ ስም ግን በገለልተኛ አካላት ተመርምረው ወይ ይፀድቃል አልያም ይከለከላሉ።

በጀርመን እና ዴንማርክ በሁለቱም ሀገራት የተከለከሉ ስሞችን ስንመለከት ቴለር፣ አሽሊ፣ ሞርጋን እና ጆርዳን ይጠቀሳሉ።

የተወሰኑ ሀገራት ደግሞ ምንም ዓይነት ፋይዳ ወይም መሰረት የሌላቸውን ስሞች ለህፃናት እንዳይወጡ ይከለክላሉ።

ፈረንሳይ እንደዚህ ዓይነት ስሞችን የሚያወጡ ሰዎችን በፍርድ ቤት ትጠይቃለች።

ለምሳሌ የእርስዎን ልጅ ስትሮበሪ (እንጆሪ) ብለው ስም ማውጣት ቢፈልጉ በፈረንሳይ ሀገር የልጅዎ ስም ሆኖ አይመዘገብም።

ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ሜክሲኮ እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ልጆች ጥቃት አድራሽ ወይም በደል አድራሽ መሆናቸውን የሚገልፁ ስሞች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ይከለክላሉ።

ለአብነትም ከተከለከሉት ስሞች መካከል፦

ልዑል ዊሊያም - በፈረንሳይ

ኦሳማ ቢን ላደን እና አዶልፍ ሂትለር - በጀርመን

አነስ - በዴንማርክ

ኤልቪስ እና ሜታሊካ - በስዊድን

ራምቦ፣ ስኮርተምእና ባትማን - በሜክሲኮ

ሴክሹዋል ኢንተርኮርስ እና ስሜሊ ሄድ - በማሌዥያ

ፈፅሞ ለህጻናት መውጣት የሌለባቸው ስሞች ናቸው።

አንዳንድ ሃገራት ደግሞ ህፃናት በስማቸው ምክንያት ጥፋተኛ ተደርገው እንዳይቆጠሩና ትንኮሳ እንዳይፈፀምባቸው ለማድረግ ህግ ያወጣሉ።

ለምሳሌ ስዊዘርላንድ ይሁዳ የሚለው ስም አገልግሎት ላይ መዋል የለበትም ብላለች።

ያሳለፍነው ጥቅምት ወር አንድ የጀርመን ዳኛ ወላጆች ልጃቸውን ሉሲፈር ብለው ስም እንዳያወጡለት ከልክለዋል።

ኒውዚላንድም ከዚህ በፊት እንደዚህ ዓይነት ስሞች እንዳይወጡ በ2013 የተከለከሉ ስሞችን ይፋ አድርጋ ነበር።

ስዊዘርላንድ በቅዱሳን መፃህፍት በሰይጣናዊ መልኩ የተፈረጁ ስያሜዎችን ለህፃናት እንዳይወጡ አግዳለች።

ሳዑዲ ዓረቢያም ከባህል ወይም ከሃይማኖታዊ አገላለጾች ጋር የሚፃረሩ ስሞች በሀገሪቱ ለህፃናት እንዳይሰየሙ አውጃለች።

በዚህ መልኩ በሃገራት ክልከላ የተጣለባቸው ስሞችን ለመጥቀስ፦

ይሁዳ - በስዊዘርላንድ

ሉሲፈር - በስዊዘርላንድና ኒውዚላንድ

መልዓክ (ኤንጅል) - በሳዑዲ ዓረቢያ የተከለከሉ ስሞች ናቸው።

ማሌዥያ ደግሞ ከፍጥረታት ጋር የተገናኙ ስሞችን ወላጆች ለልጆቻቸው ማውጣት የለባቸውም ያለች ሲሆን፥ ለምሳሌ እባብ እና ድብ የተከለከሉ ናቸው።

በአይስላንድ ደግሞ የህፃናት ስሞች መጨረሻቸው ላይ ማካተት ያለበትን ሰዋሰዋዊ ህግ መከተል አለበት።

ከዚህም ውጭ ስሞች የአይስላንድ ፊደላትን ያሟሉ መሆን አለባቸው ብላለች ሀገሪቱ።

ከዚህ ውጭ እንደ ሲ፣ ኪው፣ ኤ እና ደብልዩ ያሉ ፊደላትን ያካተቱ የሚከተሉት ስሞች በሀገሪቱ ለህፃናት እንዳይወጡ ተከልክልዋል

ዞይ (Zoe)

ሃሪዬት (Harriet)

ደንካን (Duncan)

ኤንሪኬ (Enriqu) እና

ለድዊግ (Ludwig) ይገኙበታል።

ስዊዘርላንድ የሴቶችን ለወንዶች የወንዶችን ለሴቶች ወይም የአያትን ስም ለልጅ ልጅ መጠቀምንም ትከለክላለች።

ኖርዌይም ይህን ህግ የምትከተል ሲሆን ሃንሰን፣ ጆሃንሰን፣ እና ኦልደን የሚሉ ስሞች ለህፃናት እንዳይወጡ አግዳለች።

የተወሰኑ ሀገራት ደግሞ የኩባንያ ስያሜዎችን ለህፃናት እንዳይወጡ ይከለክላሉ።

ለምሳሌ

ፌስቡክ - በሜክሲኮ

ኢኪያ -በስዊድን

መርቼዲስ፣ ኑቴላ እና ሚኒ ኩበር - በፈረንሳይ

ቻኔል - በስዊዘርላንድ

ለህፃናት እንዳይወጡ ክልከላ ከተጣለባቸው የኩባንያ ስሞች መካከል ይጠቀሳሉ።

 

 

 

www.indy100.com