የ8 ዓመቱ ልጅ በሳዑዲ አረቢያ አውራ ጎዳና ላይ መኪና ሲያሽከረክር ታይቷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ8 ዓመቱ ታዳጊ በሳዑዲ አረቢያ አውራ ጎዳና ላይ መኪና ሲያሽከረክር ታይቷል።

ይህንን ተከትሎም የሳዑዲ አረቢያ ፖሊስ በጄዳህ አካባቢ የ8 ዓመቱ ልጅ መኪና እንዲያሽከረክር በማድረግ ከጎኑ ተቀምጦ የነበረው ግለበስ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

የቀይ ባህር ከተማ ትራፊክ ፖሊስ ቢሮ እንዳስታወቁት፥ ህጻኑ ልጅ ሲያሽከረክረው የነበረው መኪናም ለአንድ ወር በቁጥጥር ስር አንዲውም ተደርጓል።

በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ላይ የተለቀቀው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ከሆነ ህጻኑ ልጅ ተሽከርካሪውን በፍጥነት በማሽከርከር ላይ እያለ አንድ ትልቅ ሰው የተጓዦች መቀመጫ ላይ አጠገቡ ተቀምጧል።

ቪዲዮው በማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ ላይ መለቀቁን ተከትሎም ፖሊስ ወዲያው እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀሱን ነው ያስታወቀው።

ፖሊስ ባደረገው ክትትልም ህጻኑ ልጅ መኪናውን እንዲነዳ አድርጓል የተባለውን ሰው በቁጥጥር ስር አውሎታል።

በሳዑዲ አረቢያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 ብቻ 533 ሺህ የትራፊክ አደጋዎች የደረሱ ሲሆን፥ 9 ሺር 300 ሰዎች ላይ የሞት እንዲሁም 38 ሺህ ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሷል።

ምንጭ፦ www.bbc.com