በየቀኑ 20 ብርጭቆ ሻይ የሚጠጣው ግለሰብ ስሙን በሚወደው ሻይ ስያሜ በይፋ ቀይሯል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በየቀኑ 20 ብርጭቆ ሻይ የሚጠጣው ግለሰብ ስሙን በሚወደው ሻይ ስያሜ በይፋ በዲድፖል ህጋዊ ሂደት ቀይሯል።

ናታን ዴሬክ ጋርነር የሚባለው ግለሰብ የመሃል ስሙን በሚወደው የሻይ ምርት በህጋዊ ሂደት በማስቀየር “ናታን ዮርክሻየር ቲ ጋርነር” ተብሏል።

ግለሰቡ ይህን ያደረገው “ዮርክሻየር ሻይ”ን በጣም ከመውደዱ የተነሳ በየቀኑ 20 ብርጭቆ ሻይ መጠጣት ከጀመረ በኋላ ነው።

ጋርነር አንድ ቀን ስራ ላይ እያለ ከስራ ጓደኞቹ መካከል አንደኛዋ “አንተ ከመካከላችን ሻይ በጣም አብዝተህ ስለምትጠጣ ስምህን በምትጠጣው ሻይ ስያሜ ብትቀይረው ጥሩ ነው” ብላ እንደቀለደችው እና ሀሳቡ በልቡ እንደቀረ ይናገራል።

ይህ ንግግር በውስጡ ትልቅ ሀሳብ እንዳለው አስቤ ነበርም ብሏል ጋርነር።

በዕለቱ ምሳ ሰዓት ላይ ስልኩን አውጥቶ የስም መቀየሪያ ይፋዊ የህግ ድረገፅ ላይ አስገብቶ ለመቀየር ጥያቄ ያቀርባል።

ስሙንም ናታን ዴሬክ ጋርነር የነበረው ናታን ዮርክሻየር ቲ ጋርነር ተብሎ እንዲቀየር አድርጓል።

york.jpg

ስሙን በሚያመርቱት በሻይ ስም እንደቀየረ እና የምርታቸው አፍቃሪ መሆኑን የሰሙት የዮርክሻየር ሻይ ኩባንያ ሃላፊዎችም በነገሩ ይገረማሉ።

ሃላፊዎቹ ጋርነር ለኩባንያቸው የሰጠው ክብር እንዳስደሰታቸው እና ሃሮጌት በሚገኘው ዋና መስሪያ ቤታቸው እንዲመጣ እንደጠየቁትም አብራርቷል።

በዋና መስሪያ ቤቱ ተገኝቶም የኩባንያው ሰራተኞች ባመረቱት ሻይ ተሰርቶለት ትኩሱን እንዲቀምስ ጋብዘውታል።

የዮርክሻየር የሻይ አምራች ኩባንያ የምርት መለያ ዘርፍ ዋና ስራ አስኪያጅ ላውራ በርተን፥ ወደ ኩባንያቸው መጥቶ የሻያቸውን ጣዕም እንዲቀምስ እና ሰራተኞችን እንዲገናኝ በፍጥነት እንደጠሩት ተናግረዋል።

ለሚያመርቱት ሻይ ላሳየው ፍቅርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የ31 ዓመቱ የአርማታ ሙሌት ሰራተኛ ጋርነር በየቀኑ ብዙ መጠን ያለው ሻይ ቢጠጣም የእንቅልፍ መከልከል ችግር እንዳላጋጠመው ተናግሯል።

 

 

 

ምንጭ፦ሜትሮ