ቴሌቪዥን ላይ ባየው ዜና የ24 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ሎተሪ አሸናፊ የሆነው ግለሰብ…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሎተሪ እየገዛ እድለኛነቱን የማያረጋግጠው ግለሰብ በቴሌቪዥን ዜና ምክንያት የ24 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ተሸላሚ ሆኗል።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፤ በኒውዮርክ የሚኖረው ጂሚ ስሚዝ ማታ ላይ ቤቱ ውስጥ የቴሌቪዥን ዜና እየተመለከተ ነበር።

ከዜናው መካከል በፈረንጆቹ 2016 ግንቦት 25 የወጣ የሎተሪ ዕጣ አሸናፊ ሰው እስካሁን አለመገኘቱን የሚገልፀው ይገኝበታል።

በዚህ ጊዜ ስሚዝ ሁል ጊዜ ሎተሪ እየቆረጥኩ አስቀምጣለሁ፤ እስቲ ድንገት ላረጋግጠው ብሎ የአሸናፊውን ቁጥር ይዞ ማመሳከር ጀመረ።
በዚህ ጊዜ ያልጠበቀውን ነገር አገኘ።

ይኸውም 05-12-13-22-25-35 የሚለው የአሸናፊ ዕጣ ቁጥር እሱ ከያዘው የሎተሪ ቲኬት ቁጥር ጋር አንድ ይሆናል።

ይህን ያላመነው ስሚዝ እንዲህ አለ “ ትንፋሼን ሰበሰብኩ፤ መስኮት ከፈትኩ ደነገጥኩም” ነው ያለው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1960ዎቹ ጀምሮ የሎተሪ ቲኬት እየቆረጠ እንደሚያከማች እንጂ አንድም ቀን እድለኛነቱን ለማወቅ የእድል ቁጥሮችን አመሳክሮ እንደማያውቅ ተናግሯል።

ጊዜ ሲኖረኝ እድል አላቸው የላቸውም የሚለውን ለማረጋገጥ እሞክራለሁ በሚል ብዙ ጊዜ መቆየቱን ነው ያነሳው።

ስሚዝ የሁለት ልጆች አባት እና የ12 ልጆች አያት ሲሆን፥ በደረሰው ገንዘብ ምን ማድረግ እንደሚገባ አጠቃላይ ቤተሰቡ እንደሚመክርበት ገልጿል።

ምንጭ፦ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል