የሚኔሶታው አትክልተኛ ከ10 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ካሮት በማሳደግ ስሙን በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ አስፍሯል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የሚኔሶታ ነዋሪው አትክልተኛ በዓለም ግዙፉን ካሮት በማሳደግ ስሙን በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ላይ አስፍሯል።

ክርስቶፈር ኳሊ በኦትሴጎ በሚገኘው የአትክልት ስፍራው ነው 10 ነጥብ 18 ኪሎ ግራም ክብደት ያለውን ግዙፍ ካሮት ማሳደግ የቻለው።

ኳሊ ካሮቱን ለማሳደግ ፅኑ ፍላጎት የነበረው ሲሆን አንድ ጊዜ ሞክሮ አልተሳካለትም።

በሁለተኛው ሙከራው ፍላጎቱን ያሳካ ሲሆን፥ ለዚህም አፈር፣ ዘር፣ የአየር ሁኔታ እና በትንሹም ቢሆን እድል እንዳገዙት ተናግሯል።

የአትክልተኝነት እውቀት እና ፍላጎቱ የለኝም ነበር፥ በዓለም ያሉ አትክልተኞች የሚያደርጉትን ስራ በመቅሰም ነው ስራውን የጀመርኩት ይላል ኳሊ።

"እያንዳንዱ እውቅ የዓለም አትክልተኛ ብትጠይቀው አንድን አትክልት ለማሳደግ ትክክለኛ አፈር ወሳኝ መሆኑን ይነግርሃል"  ነው ያለው።

በዚህ ስራው የቀጠለው ኳሊ ከዚህ ቀደም በግዝፈቱ 9 ነጥብ 12 ኪሎ ግራም ይመዝን የነበረውን ካሮት በ1 ነጥብ 06 ኪሎ ግራም የሚበልጥ ካሮት በማሳደግ የክብረ ወሰኑ ባለቤት ሆኗል።

በቀጣይም በግዝፈታቸው በዓለም ቀዳሚ የሆኑ ዱባ ወይም ቲማቲም ለማሳደግ ትኩረት ማድረጉን ገልጿል።

ምንጭ፦ዩናይትድ ፕረስ አንተርናሽናል