በቀዶ ጥገና መልክ እና ፎቶግራፋቸው የተለያየው ቻይናውያን በረራ ተከልክለዋል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 30 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ባደጉት ሃገራት በተለይም በወጣት ሴቶች ዘንድ ገጽታን በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና መቀየርና ማሳመር አሁን አሁን የተለመደ ጉዳይ እየሆነ ነው።

ይህ ሁኔታ በእስያ ሃገራት በተለይም በቻይና እና ጃፓን ሴቶች ዘንድ በተደጋጋሚ ይስተዋላል።

ቀዶ ጥገናውን የሚሰሩ ታዋቂ ክሊኒኮች ደግሞ ባህር ተሻግረው ለሚመጡ ደንበኞቻቸው፥ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ሰርተፊኬት ያዘጋጃሉ።

ይህ ሰርተፊኬት ታዲያ የሰዎቹን ማንነት፣ የፖስፖርት ቁጥር፣ በስፍራው የቆዩበት ጊዜ፣ የሆስፒታሉን መገኛና ስም እንዲሁም ማህተም ያረፈበት ነው።

ይህ መሆኑ ደግሞ ደንበኞቹ በአውሮፕላን ማረፊያ የሚያጋጥማቸውን ጣጣ ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሏል።

በዚህ መልኩ የተዘጋጀው ሰርተፊኬት ግን ከሰሞኑ ከደቡብ ኮሪያ ወደ ቻይና ለማምራት የተሰናዱ ቻይናውያንን አላገዘም።

ሶስቱ ሴቶች ቀዶ ጥገናውን ከተሰሩ በኋላ የተወሰኑ ቀናት ፊታቸውን በፋሻ ተጠቅልለው መቆየት ይኖርባቸዋል።

ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ሲያቀኑም ፊታቸው እንዳበጠና በፋሻ እንደተጠቀለለ ነበር።

ይህ መሆኑ ደግሞ በአውሮፕላን ማረፊያው ማንነታቸውን ለመለየት አዳጋች አድርጎታል ነው የተባለው።

ፓስፖርታቸው ላይ ያለው የመጀመሪያ ፎቶና አሁን በአካል የሚታየው ያበጠና የታሸገ ፊት፥ በመሳሪያም ሆነ በሰራተኞቹ ተመሳሳይነት የሌለው ሆኖ ተገኝቷል።

“ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” የሆነባቸው ሰራተኞችም ሶስቱን ቻይናውያን ባላችሁበት ቆዩ በማለት ለጊዜው በረራ ከልክለዋቸዋል።

ይህ መረጃ እስከወጣበት ጊዜ ድረሰም መንገደኞቹ ወደ ቻይና ያልተመለሱ ሲሆን፥ በፊታቸው ማበጥ ሳቢያም በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆነዋል።

አንዳንዶቹም ይህን ያበጠ ፊት አይቶ ማንነትን መለየት ለወላጅም ከባድ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

 


ምንጭ፦ ኦዲቲ ሴንትራል