የእንጀራ ድርቆሽ ቺፕስ የስራ እድል እየፈጠረ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 30 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ብቻ ከሚመረተው ጤፍ የሚሰራው የእንጀራ ድርቆሽ በአብዛኛው መንገድ ለሚወጣ ዘመድ አዝማድ የሚዘጋጅ ምግብ ነው።

በተለይም ወደ ገዳምና መሰል አካባቢዎች ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን በስንቅነት የሚያገለግለው ድርቆሽ፥ ከስንቅነት አልፎ ተፅዕኖ ወደ መፍጠር እያመራ ነው ተብሏል።

እንጀራው ከተጋገረ በኋላ በፀሃይ አማካኝነት ደርቆ የሚዘጋጀው ድርቆሽ፥ ለግል ፍጆታ ከመዋል አልፎ ለገበያ ሊቀርብ ነው።

ይህ መሆኑ ደግሞ ከፍ ያለ ማህበራዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረው፥ ቤከሪ ኤንድ ስናክ በተሰኘ ድረ ገጽ ላይ የወጣው መረጃ ያመላክታል።

በድረ ገጹ የወጣው መረጃ ኢትዮጵያዊው አሉላ ክብሮም ከአሜሪካዊት ባለቤቱ ቫለሪ ቦውደን ጋር በመሆን፥ “ድርቆሽን ይመገቡ” በሚል ድርቆሽ አቅራቢ ኩባንያን አቋቁመዋል።

ስራውን በይፋ ያልጀመረው ይህ ኩባንያ ድርቆሽን ከኢትዮጵያ ባለፈ በቀሪው አለም በማስተዋወቅ፥ ያለውን ማህበራዊ ፋይዳ ከፍ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑም ተነግሯል።

አዲስ አበባ የሚኖሩ ሁለቱ ጥንዶች ታዲያ በዚህ አማካኝነት የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከመቅረፍ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የማገዝ እቅድም አለን ብለዋል።

ተጋግሮ ደረቅ ያለውን ካለው እንጀራ የሚገኘውን ድርቆሽ በቺፕስ መልክ በአራት አይነት ጣዕም በማዘጋጀት ወደ ተቀረው አለም በመላክ ለሴቶች የስራ እድል መፍጠርና ገጽታውን ማስተዋወቅም እቅዳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ድርቆሹን በጥቂት በጥቂቱ በመቆራረጥም በጥቂት የገበታ ጨው፣ በተፈጨ ሰሊጥ፣ በነጭ ሽንኩርት እና ሚጥሚጣ ጣዕም ለተጠቃሚዎች እናቀርባለንም ነው ያሉት።

በጥቂቱ የተቆራረጠው ድርቆሽ አራቱ ማጣፈጫና ቅመሞች ተጨምሮበትና በእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ ላይ ጥቂት እሳት ከተመታ በኋላ፥ በቺፕስ መልክ ታሽጎ ለተጠቃሚ የሚቀርብ ይሆናል።

በቀጣዩ የፈረንጆች አመትም ድርቆሹን ወደ ለንደን ለመላክ ተዘጋጅተናል ብላለች ቦውደን፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በቺፕስ መልክ የሚያዘጋጁት ድርቆሽ የኤክስፖርት መስፈርትን ሊያሟላ ይገባል።

አሁን ላይ ለስድስት ሴቶች የስራ እድል የፈጠረው የድርቆሽን ይመገቡ ኩባንያ፥ ወደ ፊት በርካታ ሴቶችን በመቅጠር የሴቶችን ተጠቃሚነት የማሳደግ እቅድ አለው ተብሏል።

ጤፍና ኢትዮጵያን በሰፊው አስተዋውቆ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይቻል ዘንድ ግን፥ የመስሪያ እቃዎች አቅርቦትን ጨምሮ ሌሎች መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች ሊሟሉ እንደሚገባም ቦውደን ትገልጻለች።

እስከዛው ግን ባለን እየተጠቀምን የሴቶችን ብሎም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንሰራለንም ትላለች።

 


ምንጭ፦ bakeryandsnacks.com