በህይወት 150 ዓመት ይኖራል ተብሎ የሚገመተው ኤሊ 67ኛ የልደት ቀኑን አከበረ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በህይወት 150 ዓመት ይኖራል ተብሎ የሚገመተው ኤሊ 67ኛ የልደት ቀኑን አክብሯል።

በኢኳዶር ጋላፓጎስ ደሴት የሚኖረው ሁጎ በመባል የሚጠራው ትልቁ ኤሊ፥ ኬክ በመብላት የልደት በዓሉን በአውስትራሊያ ሬፕታይል ፓርክ ነው ያከበረው።

የፓርኩ ስራ አስኪያጅ ቲም ፋልክነር፥ 67 ሻማዎች የበራለት ሁጎ በመካከለኛው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ ሲሆን፥ 150 ዓመት ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል ብለዋል።

“ሁጎ በጣም ትልቅ ኤሊ ነው፤ እሱ በትኩረት የሚቀበለውን ማንኛውንም ነገር ይወዳል” ነው ያሉት።

165 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ሁጎ ከእንግዶች ጋር በመሆን በበዓለ ልደቱ በጣም ደስ ብሎት እንዳሳለፈ ተነግሯል።

በጋላፓጎስ ደሴት የሚገኘው ኤሊ ከሌሎች እንስሳት ጋር ሲወዳደር በጣም ረጅም ጊዜ እንዳለውም ተገልጿል።

በፈረንጆቹ 2006 በ175 ዓመቱ የሞተው ኤሊ የአውስትራሊያ ባለ እድሜ ጠገቡ ተብሎ በታሪክ መዝገብ ላይ መስፈሩ ይታወሳል።

ምንጭ፦ ስካይ ኒውስ