ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል የኤሌክትሪክ ንዝረት ያለው ጫማ የሰራው ተማሪ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህንዳዊው ተማሪ ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከል የኤሌክትሪክ ንዝረት ያለው ጫማ ሰርቷል።

የ17 ዓመቱ ተማሪ ሲዳርት ማንዳላ በህንድ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ወሲባዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን በተለያዩ ምክንያቶች ያውቃል።

በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ በደሎችን እንዲቆሙና ለውጥ እንዲመጣ በሚጠይቁ ሰልፎች ላይ አብዛኛዎቹ ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ይቁም የሚል አቋም እንዳላቸው መረዳቱን ተማሪ ማንዳላ ተናግሯል።

በዚህም ችግሩን መቅረፍ የሚቻልበትን የራሱን ፈጠራ ለመስራት አልሞ ተነሳ፤ ከብዙ ጊዜ ጥረት በኋላ ሴቶች የሚጫሙትና ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው የሚከላከል ጫማ ሰርቶ ይፋ አደረገ።

ጫማው የ0 ነጥብ 1 አምፔር የኤሌክትሪክ ንዝረት ያለው በመሆኑ፥ በሴቶች ላይ ጥቃት ሊፈፅም የሚሞክር ሰው በንዝረቱ ጉዳት እንዲደርስበት የሚያደርግ ሲሆን፥ ሴቶች በአደጋ ላይ መሆናቸውን ለፖሊስ የማሳወቂያ ጥሪ አለው ተብሏል።

ማንዳላ በፊዚክስ ትምህርት ያገኘውን እውቀት ተጠቅሞ የሰራው ጫማ የተጫሙት ሰዎች ብዙ ጊዜ በሚራመዱበት ጊዜ በተገጠመለት የሃይል መሙያ መሰረት ሃይል ያጠራቅማል ነው ያለው።

የቶማስ ኤዲሰን አምፖልን ለመስራት 1 ሺህ ጊዜ የሞከረውን ተስፋ ያለመቁረጥ ጥረት በማሰብ ከ17 ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ ነው ማንዳላ ጫማውን የሰራው።

የማንዳላ የጫማ ፈጠራ አሁንም ቀሪ ስራዎች የሚጠናቀቁለት ሲሆን፥ በተለያየ ዓይነት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ እቅድ አለው።

ሆኖም የፈጠራ ውጤቱ በሀገሪቱ መንግስት ተቀባይነት ያገኛል ወይ የሚለው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ ነው።

ምንጭ፥ ኦዲቲ ሴንትራል