ሞስኮ ኤኬ-47 በመባል የሚጠራውን የጦር መሳሪያ ለሰሩት ክላሽንኮቭ ሀውልት አቆመች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ሞስኮ ኤኬ-47 በመባል የሚጠራውን የጦር መሳሪያ ንድፍ ለሰሩት ሚካሄል ክላሽንኮቭ ሀውልት አቆመች።

ክላሽንኮቭ ሩሲያ የምትታወቅበትን ኤኬ-47 የጦር መሳሪያ ንድፍ በመስራት ስሟን ከፍ ያደረጉ ሰው ናቸው።

በዓለም ላይ ከሚገኙ የጦር መሳሪያ ዓይነቶች በብዛት አንድ አምስተኛ ድርሻውን የሚይዘው ይህ የጦር መሳሪያ፥ በተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ ሃይሎች፣ በአሸባሪዎች እና በአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች ተመራጭ ነው።

የንድፉ ባለቤት ክላሽንኮቭ ሚካሄል በሩሲያ በረዷማ ስፍራ ሳይቤሪያ ከአርሶ አደር ቤተሰቦቹ በ1919 ተወለዱ።

የአርሶ አደር ልጅ እንደመሆናቸውም በመጀመሪያ የነበራቸው እቅድ የእርሻ መሳሪያ ማዘጋጀት ነበር፤ ሆኖም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመቅስቀሱ ወደ ውትድርናው እንዲገቡ ተገደዱ።

ብርያንስክ በተባለ ስፍራም በፈረንጆቹ 1941 በተደረገ ጦርነት በደረሰባቸው ጉዳት፥ ብዙ ጊዜ በሆስፒታል ውስጥ አሳለፉ፤ በሆነ አጋጣሚም ሌሎች የጦር ሰራዊት በያዙት የጦር መሳሪያ ምክንያት የበታችነት እየተሰማቸው መሆኑን ይረዳሉ።

በዚህ ምክንያት የራሳቸውንን የጦር መሳሪያ ለመስራት ባቀዱት መሰረት የሶቪየት ወታደራዊ ሃይል ክላሽንኮቭን በዓይነቱ የተለየ የጦር መሳሪያ እንዲያዘጋጁ መደባቸው።

የመጀመሪያው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ፤ በመጨረሻም በፈረንጆቹ 1947 ስኬታማ የሆነ “አቭቶማት ክላሽንኮቭ(19)47” የተባለ የጦር መሳሪያን ሰሩ።

የጦር መሳሪያው የተሰራበትን ዓመት እና የፈጠራ ባለቤቱን ስም በአንድ ላይ በመያዝ “ኤኬ-47” የሚል የበአህፅሮት ስያሜን ያዘ።

በበረሃ፣ በቀዝቃዛ እና በሌሎችም ቦታዎች ኢላማ ጠብቆ በመምታት ተመራጭ የጦር መሳሪያ በመሆኑ፥ በዓለም ዝናው ከፍ ያለ ነው፤ አተካኮሱም በቀላሉ የሚለመድ ተወዳጅነቱን ከፍ አድርጎታል።

የጦር መሳሪያው በሶቪዬት ህብረት ወታደራዊ ተቋም በብዙ ቁጥር ተመርቶ ለራሳቸው የጦር ሰራዊት እና በርዕዮተ ዓለም እና በውጊያ ከጎናቸው ለተሰለፉ አቢዮታዊ የእስያ እና የአፍሪካ የጦር ቡድኖች እንዲዳረስ ተደረገ።

ሞስኮ ሌሎች ሀገራትም ኤኬ-47 የጦር መሳሪያ ንድፍን ወስደው በየአካባቢያቸው እንዲያመርቱ ፈቀደች።

የኤኬ-47 የጦር መሳሪያ ምስል በሞዛምብክ ሰንደቅ ዓላማ እና በሄዝቦላህ አርማ ላይ ያለ ሲሆን፥ የጥይቱ መስል ደግሞ በዚምባብዌ ወታደሮች የደንብ ልብስ ላይ ይገኛል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ስለ ክላሽንኮቭ መሳሪያ ሲናግሩ፥ የህዝባችን የፈጠራ አቅም እጅግ የላቀ መሆኑን ያሳየ ነው ይላሉ።

የሀገሪቱ የባህል ሚኒስትር ቭላድሚር ሜዲንስኪ በበኩላቸው፥ ኪላሽንኮቭ የጦር መሳሪያ የሩሲያ የባህል መለያ ነው ብለውታል።

ክላሽንኮቭከመሞታቸው በፊት ለሩሲያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ መሪ ፓትሪያሪክ ኪሪል አንድ የንስሃ ደብዳቤ ልከው ነበር።

በደብዳበው ውስጥ “እኔ ሚካሄል ክላሽንኮቭ የሰራሁት የጦር መሳሪያ የሰዎችን ህይወት ለመንጠቅ አላማ ከዋለ፥ ለሰዎች መሞት ተጠያቂው እኔ ነኝ” የሚል መልዕክት አለ።

ፓትርያርኩም በምላሻቸው “የጦር መሳሪያውን በመጠቀም ለሚጠፋው ህይወት ተጠያቂዎች የጦር መሳሪያውን ለሰዎች እልቂትየሚያውሉት እንጀ አንተ አይደለህም” የሚል መልዕክት ልከውላቸዋል ተብሏል።

ክላሽንኮቭ በፈረንጆቹ 2013 በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

 

 

 

 

 

ምንጭ፦አሶሼትድ ፕረስ