ህንዳዊቷ አዛውንት ለ60 ዓመታት በሻይና በውሃ ብቻ ነው የኖርኩት ይላሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህንዳዊቷ የ75 ዓመት አዛውንት “ያለፉትን 60 ዓመታት ምንም አይነት ጠጣር ምግብ ሳልመገብ ነው ነው የኖርኩት” ይላሉ።

ሳራስዋቲ ባይ የተባሉት የ75 ዓመቷ አዛውንት ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ሩዝም ይሁን ሌላ ጠጣር ምግብ በልተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

“አልፎ አልፎ በሳምንት አንድ ቀን አንዲት ፍሬ ሙዝ በልቼ አውቃለው፤ ከዚያ ውጭ ግን እስካሁን በሻይ እና በውሃ ብቻ ነው እየኖርኩ ያለውት” ብለዋል።

ሳራዊቲ ከ60 ዓመት በፊት የመጀመሪያ ልጃቸው እስከሚወለድ ልክ እንደሌላው ሰው ትክክለኛ አመጋገብ ሲጠቀሙ እንደነበረ የሚናገሩ ሲሆን፥ የመጀመሪያ ልጃቸውን እንደወለዱ ግን በታይፎይድ ኢንፌክሽን ይጠቃሉ።

በጊዜውም ምግብ በሚመገቡበት ጊዜ ሆዳቸው አካባቢከፍተኛ ህመም የሚሰማቸው ሲሆን፥ ህመሙን ፍራቻም ምገብ መመገብ ያቆማሉ።

ከረጅም ቆይታ በኋላ ሻይ በመጠኑ መጠጣት የጀመሩት ሳራስዋቲ፥ የምግብ ፍላጎታቸው ግን ዳግም መመለስ እንዳልቻለ ነው የሚነገረው።

ሳራስዋቲ ምግብ እንዲመገቡ በባለቤታቸው እና በሌሎች ዘመዶቻቸው የተለያዩ ተማጽኖዎች ቢቀርብላቸውም እሳቸው ግን ምግብ አልቀምስ ብለው እስካሁን ቆይተዋል።

“በሻይ እና በውሃ ብቻ መኖር ይስማማኛል” ያሉት አዛውንቷም እስካሁን በዚሁ መልኩ ኖሯቸውን እየገፉ ነው።

ምንጭ፦ www.odditycentral.com