የበርሊን አየር መንገድ በአንድ ቀን 200 አብራሪዎቹ ታመናል በማለታቸው ተጓዦችን አስተጓጉሏል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የበርሊን አየር መንገድ በአንድ ቀን 200 አውሮፕላን አብራሪዎች ታመናል በማለታቸው ተጓዦችን አስተጓጉሏል።

አየር መንገዱ ትናንት በነበረው የበረራ መርሃ ግብር ተጓዦቹን ወደ የሀገራቱ ለማድረስ ወደ አብራሪዎቹ ሲደውል 200 አብራሪዎች ታመናል የሚል ሪፖርት አቅርበውለታል።

የበርሊን አየር መንገድ ከፍተኛ ኪሳራ ላይ የሚገኝ አየር መንገድ ነው።

ከአየር መንገዱ 1 ሺህ 500 አበራሪዎች መካከል 200 ያህሉ ትናንተ የበረራ ፈረቃ ቢኖርባቸውም አልተገኙም።

ታመናል ባሉት የአውሮፕላን አብራሪዎች በስራ ገበታቸው አለመገኘት ብቻ 100 በረራዎች ተሰርዘዋል።

ይህም በተለያዩ የጀርመን አውሮፕላን ማረፊያዎች ከፍተኛ ቀውስን ፈጥሯል ነው የተባለው።

የበርሊን አየር መንገድ የኦፕሬሽን ዘርፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኦሊቨር ኢፈርት እንደተናገሩት፥ የትናንቱ ክስተት ለአየር መንገዳቸው ከፍተኛ የህልውና ስጋት ነው።

ቢልድ የተባለ ዕለታዊ ጋዜጣ ባወጣው መረጃ ደግሞ አውሮፕላን አብራሪዎቹ ታመናል በሚል በስራ ገበታቸው ላይ አለመገኘታቸው፥ በአየር መንገዱ ደስተኛ ባለመሆናቸው የተቃውሞ ምልክት ነው የሚሉ ሰዎች እንዳሉ በዕትሙ ይዞ ወጥቷል።

የአውሮፕላን አብራሪዎች ማህበር ደግሞ መረጃው ሀሰት ነው ብሏል።

አየር መንገዱ ዛሬ የበረራ ፈረቃ ያለባቸው 149 አብራሪዎችና የበረራ ሰራተኞች፥ በህመም ምክንያት እንደማይችሉ ማሳወቃቸውን ገልጿል።

በጀርመን በግዝፈቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው በርሊን አየር መንገድ ላለፉት ዓመታት ያለበትን እዳ ባለመክፈል ኪሳራ ውስጥ ይገኛል።

በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ያለው የአቡ ዳቢው ኢቲሃድ አየር መንገድ ያደርግለት የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ አቋርጧል።

የበርሊን አየር መንገድ ያለበትን ኪሳራ ለማካካስና ስሙን ለማቃናት ባለሃብቶች እንዲቀላቀሉት ያወጣው ጨረታ ሊዘጋ ጥቂት ቀናት ቢቀሩትም በኦፕሬሽን ዘርፍ እየገጠመው ያለው ችግር ሌላ ፈተና ሆኖበታል።

ከመጪው የፈረንጆቹ መስከረም 25 ጀምሮም ወደ ካሪቢያን ሀገራት እና ወደ አሜሪካ የሚደረጉ በርካታ በረራዎችን እንደሚሰርዝ በአፕሬሽን ዘርፍ ዋና ስራ አስፈፃሚው የውስጥ ማስታወሻ በወጣ መረጃ ተጠቁሟል።

ባሰለፍነው የፈረንጆቹ ነሃሴ 15 ቀን አየር መንገዱ ያለበትን እዳ መክፈል እንደማይችል ካሳወቀ ጊዜ ጀምሮ ቲኬት የገዞ ደንበኞች ግንዘባቸው እንደሚመለስላቸውም አሳውቋል።

ምንጭ፦thewest.com.au