በሳዑዲ መንገድ ላይ ሲደንስ የነበረው ታዳጊ በቁጥጥር ስር ውሏል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሳዑዲ አረቢያ ከሰሞኑ አንድ ታዳጊ እንደ አውሮፓውያኑ በ1995 በሎስ ዴል ማር ተቀንቅኖ ተወዳጅነትን ባተረፈው “ማካሬና” ሙዚቃ መንገድ ላይ ሲደንስ የሚያሳየው ምስል ተለቆ በርካቶች ተመልክተውታል።

የሀገሪቱ ፖሊስ ግን ይህ ታዳጊ “በህዝብ ፊት ተገቢ ያልሆነ ባህሪ” አሳይቷል፤ የትራፊክ ፍሰትንም አስተጓጉሏል በሚል በቁጥጥር ስር አውሎታል።

በጂዳ ከተማ በአንድ ግለሰብ የተቀረፀው ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች በርካቶች የተቀባበሉት ሲሆን፥ ፖሊስ የታዳጊው ዳንስ ከሀገሪቱ ወግና ባህል ያፈነገጠ ነው በሚል ጠርጥሮ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር አውሎታል።

ታዳጊው በተሽከርካሪዎች መስመር ላይ በመግባት ጭምር በመደነሱም የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ማወኩን ነው ፖሊስ የገለፀው።

ስሙ እና ዜግነቱ ያልተጠቀሰው ታዳጊ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ሊተላለፍበት የሚችለው እርምጃ አለመገለፁን ሬውተርስ ዘግቧል።

የሳዑዲ ፖሊስ ባለፈው ሀምሌ ወር አብደላህ አል ሻሃራኒ የተባለውን ሙዚቀኛ እና ተዋናይ በሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ያልተገባ ዳንስ አሳይቷል በሚል በቁጥጥር ስር አውሎታል።

አንድ እጅን ከፍ አድርጎ በማጠፍ ፊትን በዚያ ውስጥ መሸፈን በሳዑዲ የተከለከለ ተግባር ነው።

የሀገሪቱ ብሄራዊ የአደንዛዥ እፅ ቁጥጥር ኮሚቴ ይህ አይነቱ ተግባር አደንዛዥ እፅ መውሰድን ያበረታታል።

አል ሻሃራኒ ከጥቂት ቆይታ በኋላ የተለቀቀ ሲሆን፥ ህዝቡን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ተደርጓል።

በያዝነው የፈረንጆቹ አመት በሪያድ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሀገሪቱ ባህላዊ የጎራዴ ዳንስ መሳተፋቸው ይታወሳል።

 

 

 

ምንጭ፦ www.msn.com/

 

 

 


በፋሲካው ታደሰ