በጣሊያን ከንቲባው ቁምጣ በመልበሳቸው ምክንያት ከመዝናኛ ክለብ እንዲወጡ ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰሜናዊ ጣሊያን በባህር ዳርቻ አጠገብ ወደሚገኝ የምሽት መዝናኛ ቤት ያመሩት ከንቲባ ቁምጣ በመልበሳቸው ምክንያት ከክለቡ እንዲወጡ ተደርጓል።

ከንቲባው ወደ መዝናኛ ክለቡ እንዳይገቡ የተከለከሉት በእራት ፕሮግራም ደንበኞች እንዲለብሱት የተቀመጠውን የልብስ አይነት ባለመልበሳቸው ነው ተብሏል።

በቱስካኒ የባህር ዳርቻ ከተማ የሆነችው ቫያርጂዮ ከንቲባ የሆኑት ጆርጂዮ ዴል ሂንጋሮ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ወደ መዝናኛ ክለቡ እንዳይገቡ መከልከላቸው እንዳበሳጫቸው አስፍረዋል።

ስለ መዝናኛ ክለቡ የአለባበስ ስነ ስርአት (ድሬስ ኮድ) አልተነገረኝም ያሉት ከንቲባው፥ “ወደ ምግብ ቤቱ ያመራሁት ከባለስልጣናት ጋር ለመመገብ ሳይሆን ከጓደኞቼ ጋር በመሆኑ ቁምጣ ለብሻለሁ” የሚል ፅሁፋቸውንም የፌስቡክ ገፃቸው ላይ ለጥፈዋል።

ክለብ ናውቲኮ የተሰኘው የምሽት መዝናኛ ክለብ በበኩሉ፥ በተፈጠረው ነገር ማዘኑንና ከንቲባውን ልዩ ጥቅም የሚያስገኝ የአባልነት መታወቂያ እንደሚሰጠው አስታውቋል።

ከንቲባው “ከጓደኞቼ ጋር በረንዳ ላይ ተቀምጠን ስንጨዋወት የተበሳጨ የሚመስል አስተናጋጅ መጣና ረጅም ሱሪ አለመልበሴንና ከጓደኞቼ ጋር መቆየት እንደማልችል ነገረኝ” ብለዋል።

ጆርጂዮ ዴል ሂንጋሮ ከምሽት መዝናኛ ክለቡ በለበሱት ቁምጣ ምክንያት እንዲወጡ ቢደረግም ከጓደኞቻቸው ጋር ሌላ ቦታ እራት መመገባቸውን ገልፀዋል።

“ቁምጣ ለብሰሃል” በሚል ምክንያት ከመዝናኛ ክለቡ መሰናበታቸው ግን በጣም እንዳበሳጫቸው ነው የተናገሩት።

የክለብ ናውቲኮ የመዝናኛ ክለብ አስተዳደር ክፍል ተወካይ ሙዚዮ ስካሺቲ በበኩላቸው፥ የክለቡን የአለባበስ ስነ ስርአት የተመለከቱ ሁለት ማስታወቂያዎች መግቢያ በሩ ላይ መለጠፋቸውን ተናግረዋል።

በተለጠፉት ማስታወቂያዎች ላይም ከምሽት 1 ሰዓት በኋላ የሚስተናገዱ ደንበኞች ረጅም ሱሪ ማድረግ እንዳለባቸው ያመላክታሉ ነው ያሉት።

“በተፈጠረው ነገር አዝኛለሁ፤ ለከንቲባውም ሁኔታውን ለማስረዳት እሞክራለሁ” ነው ያሉት ስካሺቲ።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

በፋሲካው ታደሰ