ካናዳዊው አባወራ ተርቦችን ለማጥፋት የለኮሱት እሳት ቤታቸውን በእሳት አያይዞታል

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 4 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ካናዳዊው ግለሰብ ተናዳፊ ተርቦችን ከመኖሪያ ቤታቸው ለማጥፋት በሚል ራሳቸውን ችግር ውስጥ ከተዋል።

ግለሰቡ ተንደር ቤይ በተባለው አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚኖሩበት ቤት ተናዳፊ ተርቦች አስቸግረዋቸዋል።

ተርቦቹ በቤቱ የውጭኛው የግድግዳ ከፍል ላይ መኖሪያ በመስራት በዚያው ጎጇቸውን ቀልሰዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ ሙሉ ቤተሰቡን አላስደተሰተምና አባ ወራው መላ ዘየዱ፤ ተርቦቹን ለማጥፋት እንደ ቀፎ የሚገለገሉበትን የቤቱን ግድግዳ በእሳት መለኮስ።

አስበውም አልቀሩም በተርቦቹ መኖሪያ ላይ ጋዝ በማርከፍከፍ በእሳት አያያዙት።

እርሳቸው በዚህ መልኩ ያያዙት እሳት ግን ተርቦቹን ብቻ ሳይሆን የቤቱን ግድግዳ በማያያዝ የእሳት አደጋ አስከትሏል።

በዚህ ሳቢያ የአካባቢው የእሳት አደጋ ሰራተኞች ወደ ቤቱ በመምጣት እሳቱን ለማጥፋት ተገደዋል።

የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከል ቡድን ሃላፊ ጆን ካፕላኒስ፥ ቤቱ ውስጥ ያልታሰበ አደጋ መከሰቱን አስረድተዋል።

በአደጋው ሳቢያም የቤቱ ግድግዳ ፈርሶ እንደገና መታደስ መጀመሩንም ተናግረዋል።

አባወራው ዋጋ ከፍለው ትምህርት ቀስመዋልም ነው ያሉት ሃላፊው።

 

 

 


ምንጭ፦ ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል