ትራምፕ የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉበት ቤት ለኪራይ ጨረታ ወጥቷል

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 4 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉበት ቤት ለኪራይ ጨረታ መውጣቱ እየተነገረ ነው።

አወዛጋቢው ፕሬዚዳንት ተወልደው የተወሰነ የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉበት መኖሪያ ቤት ኤር ቢ ኤን ቢ በተሰኘውና በኢንተርኔት የቤት አሻሻጭና አከራይ በሆነው ድርጅት አማካኝነት ነው ለኪራይ የቀረበው።

ትራምፕ የልጅነት ጊዜያቸውን ባሳለፉበት ኒውዮርክ የሚገኘው መኖሪያ ቤት ከትራምፕ ቤተሰብ ባለቤትነት ከወጣ ቆይቷል።

አሁን በድርጅቱ የወጣው ጨረታም ቤቱን መከራየት የሚፈልግ ካለ በቀን 777 የአሜሪካ ዶላር እየከፈለ መከራየት እንደሚችል ያሳያል።

በኩባንያው ገጽ ላይ የወጣው የጨረታ ማስታወቂያም፥ አጋጣሚው በተቀማጩ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ቤት ለመቆየት የተለየ መሆኑን ይገልጻል።

Trumps_NYC.jpg

ቤቱ ትራምፕ እስከ አራት አመታቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያሳለፉበት ነበር ተብሏል።

ከዚያ በኋላ ቤተሰቦቻቸው በአካባቢው የሚገኝ የተንጣለለ ቪላ ገዝተው በመዛወራቸው ምክንያት ቤቱን ለመልቀቅ ተገደዋል።

ቤቱ ዶናልድ ትራምፕ ልዕለ ሃያሏን ሃገር ለመምራት ከተመረጡ ከሁለት ወራት በኋላም ገበያ ወጥቶ 2 ነጥብ 14 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተሸጧል።

አምስት መኝታ ቤቶችን ጨምሮ ሶስት መታጠቢያ ክፍሎችን ያካተተው የትራምፕ የልጅነት ቤት፥ የመካከለኛው ዘመን የቤት አሰራር ጥበብ ያረፈበት ሀንጻ ነው።

አሁን ላይም የቤቱ ይዘት ከቀድሞው እምብዛም ያልተቀየረና ዶናልድ ትራምፕ የሚወዱት አይነት ይዘት ያለው መሆኑን አጫራቹ አስታውቋል።

ቤቱ ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን የሚኖርበት ሲሆን፥ ሳሎን በምትመስለው የመጀመሪያዋ ክፍልም የትራምፕ ሃውልት ተቀርጾ ቆሟል።

ትራምፕ በአባታቸው የተገነባውን የቀድሞ መኖሪያቸውን በድጋሚ የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ባለፈው መስከረም ወር ተናግረው ነበር።

በአንድ ጊዜ 20 ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል የተባለው ቤት፥ ከኪራይ ውጭ ለሽያጭ ስለመቅረብ አለመቅረቡ ግን የተገለጸ ነገር የለም።

መከራየት የሚፈልግ ካለም በሰከነ መንፈስ ብቻ ለመቆየት እንጅ፥ ተከራይቶ መደገስ እና መጨፈር፣ ማጨስ የቤትም ሆነ ሌሎች ለማዳ እንስሳትን ይዞ መምጣት አይፈቀድለትም።

 

 

 


ምንጭ፦ ቢቢሲ