በዓለም ደረጃዋን የጠበቀች ትንሿ ሻይ ቤት መገኛ ኢራን ሆኗል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራን ደረጃዋን የጠበቀችና በዓለም የትንሿ ሻይ ቤት መገኛ መሆኗ ተነግሯል፡፡

አንጋፋ እድሜ ያላት ሻይ ቤቷ ቴህራን ውስጥ በሺዎች በሚቆጠሩ ሱቆች መካከል ነው የምትገኘው፡፡

በካዜም ማቡትያን ባለቤትነት የምትተዳደረው "ሃጂ አሊ ደርቪሽ" የተሰኘቺው ይህች ቤት ስፋት የሁለት ሜትር ብቻ ነው፡፡

በየቀኑ በርካታ ደንበኞችን የምታስተናግድ ሲሆን በቤቷ ውስጥ ቡና፣ ሻይ እና ቸኮሌት ይሸጣሉ፡፡

አሁን በባለቤትነት የሚያስተዳድሯት ማቡትያን ሻይ ቤቷን የተረከቡት ከአባታቸው የሃጂ አሊ ማትያን ነው፤ አባታቸው ደግሞ ከቀድሞ ባለቤቷ ሃጂ ሞሃመድ ሃሰን ሸምሺሪ በ1962 እንደገዟት ተነግሯል፡፡

ከ1979 የኢራን አቢዮት በፊት ሻይ ቤቷ በአካባቢው ላሉ ሱቆች በሙሉ ሻይ አቅራቢ ነበረች፡፡

ከአቢዮቱ በኋላ በአካባቢው ያሉ ነጋዴዎች በሙሉ ራሳቸው ሻይ ማዘጋጀት ቢጀምሩም ቤቷ ስራዋን አላቋረጠችም፡፡

Tehra-teahouse_1.jpg

በተለይም የጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ገበያዋ ደርቶላታል፤ የውጭ ሀገር ዜጎችም በትንሿ ቤት ውስጥ በመስተናገዳቸው በጣም ደስተኛ መሆናቸውን በአስተያየት መዝገብ እንደሚያሰፍሩ ባለቤቷ ተናግረዋል፡፡

ሻይ ቤቷ ከሁለት ዓመት በፊት "ሃጂ አሊ ደርቪሽ" የሚል የኢንስታግራም ገፅ በመክፈት በማህበራዊ የትስስር ገፆች በማስተዋወቅ እና አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ላይ ትገኛለች፡፡

በኢንስታግራም ገፁ ላይም በየቀኑ መጥተው የሚስተናገዱ የውጭ ዜጎችና ሌሎች ፎቶግራፎች ይጋሩበታል፡፡

ምንጭ፡-ሲ ኤን ኤን