ሴት ልጃቸውን በአደጋ ያጡት ህንዳዊ የ800 ልጆች እናት ሆነዋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዶክተር ሳሮጂኒ አገርዋል ሴት ልጃቸውን ከ40 አመት በፊት ነው በመኪና አደጋ ያጡት።

ዶክተር ሳሮጂኒ የ8 አመት ልጃቸውን ማኒሻ ከኋላ አድርገው ሞተር ሳይክል ሲያሽከረክሩ ነው ከኋላቸው የሚበር መኪና የገጫቸው።

በወቅቱ ማኒሻ ወዲያውኑ ህይወቷ ሲያልፍ ዶክተር ሳሮጂኒ ይተርፋሉ።

ፈጣሪ በጣም የምወዳት ልጄን ለምን ቀማኝ እያሉ ለአመታት በሀዘን ውስጥ የቆዩት ሳሮጂ፥ አንድ ቀን ግን በርካታ የእናት ፍቅር የሚሹ ሴቶች እንዳሉ እና እነርሱን መርዳት ማኒሻን ለማስታወስ እንደሚረዳቸው ሀሳብ ብልጭ ይልላቸዋል።

ከዚያ ቀን በኋላም (እ.ኤ.አ በ1985) ባለ ሶስት ክፍል ቤታቸውን አሳዳጊ የሌላቸውን ሴቶች ለመቀበል ዝግጁ አድርገው በራቸውን ክፍት ማድረጋቸውን ይነገራሉ።

Sarojini-Agarwal-Manisha-Mandir6-750x563.jpg

እኝህ የ80 አመት አዛውንት እና ባለቤታቸው ቪ ሲ አገርዋል ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበሏት እናቷ በወሊድ ምክንያት ህይወቷ ያለፉባት መስማት የተሰናትን ህፃን ነበር።

ከዚያ በመቀጠልም ሁለት በመኪና አደጋ ምክንያት እናታቸውን ያጡ ሁለት ወጣት ሴቶች እነ ዶክተር ሳሮጂኒ ተቀላቅለዋል።

በእናቶቻቸው የተጣሉ በርካታ ልጆችም ወደ አዲሱ የዶክተር ሳሮጂኒ እና ባለቤቷ ቤት እንዲገቡ ተደርገዋል።

የሁለት ቀን እድሜ ያለው ጨቅላ ህፃን ቤታቸው በር ላይ ተጥሎ ማግኘታቸውን የተናገሩት ዶክተር ሳሮጂኒ፥ ይህም እናት ለመሆን ልጅ መውለድ ብቻ በቂ አለመሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረጉን ገልፀዋል።

ዶክተር ሳሮጂኒ እነዚህን አሳዳጊ የሌላቸው ህፃናት ሲታቀፉ በማኒሻ ያጡት የእናትነት ስሜታቸው እንደሚረካም ነው የሚናገሩት።

Sarojini-Agarwal-Manisha-Mandir2.jpg

 

ህፃናቱ ከሚያስፈልጋቸው እናታዊ ፍቅር ባሻገር ትምህርታቸውን በአገባቡ እንዲከታተሉ የቀድሞ ቤታቸውን ለቀው የተለያዩ ቤቶችን መቀያየራቸውን ገልፀው፥

በአሁኑ ወቅት የሚኖሩበት ግቢ ቤተመፅሃፍት፣ የኮምፒውተር ላብራቶሪ፣ የእደ ጥበባት ሙያ መማሪያ፣ የቅርጫት ኳስ እና ባድሜንተን ሜዳ እንዲሁም የቴሌቪዥን መመልከቻ ክፍል የተሟላለት መሆኑን አብራርተዋል።

ለስኬታማ ህይወት ትምህርት ቁልፍ መሆኑን የሚገልፁት ዶክተር ሳሮጂኒ፥ ካሳደጓቸው ልጆች መካከል በህንድ ከፍተኛ ዋጋ በሚያስከፍሉ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው አኩሪ ውጤት ያመጡት በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የባንክ ስራ አስኪያጆች፣ አስተማሪዎች እና በተለያዩ የአመራርነት ስፍራዎች ላይ የተሰማሩ ልጆች እንዳሏቸውም ይናገራሉ።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1985 በተቋቋመው ማኒሻ ማንዲር የበጎ አድራጎት ድርጅት 800 የሚጠጉ ሴቶችን ያሳደጉት ዶክተር ሳሮጂኒ እና ባለቤታቸው ሜያቸው ቢገፋም አሁንም አሳዳጊ የሌላቸውን ህፃናት ለመርዳት ፍላጎት እንዳላቸውም ነው የሚገልጹት።

Sarojini-Agarwal-Manisha-Mandir3.jpg

 

“በእያንዳንዱ አሳዳጊ የሌላቸው ህፃናት ፊት ልጄን ማኒሻን አያታለሁ” የሚሉት ሳሮጂኒ፥ “ፈጣሪ ልጄን የነጠቀኝ እነዚህ ልጆች እንዳሳድግ ስለፈቀደ ነው፤ ልጄን በመልካም ተግባር ሁሌም እያስታወስኳት እንድኖር እድሉን ስለሰጠኝም አመሰግነዋለሁ” ብለዋል። 

ዶክተር ሳሮጂኒ እና ባለቤታቸው አሳድገው ለቁምነገር ያበቋቸው ልጆች እየተመላለሱ እንደሚጠይቋቸውና፥ ጎጆ ቀልሰው ልጅ የወለዱ እንዳሉም ጠቁመዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ www.odditycentral.com/

 

 

 

 

በፋሲካው ታደሰ