በአሜሪካ የቬርሞንት ባለስልጣናት በዛፎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ለጠቆመ 100 ዶላር ሽልማት አዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የቬርሞንት ግዛት ስር የምትገኘው አነስተኛዋ ዌስትሩትላንድ ከተማ አስተዳዳሪዎች በአካባቢው የሚገኙ ዛፎችን ህልውና ለመታደግ ለየት ያለ ሽልማት አቅርበዋል።

የከተማዋ አስተዳዳሪዎች በከተማ የተተከሉ በርካታ የዛፍ ቅርንጫፎች ግንድ በህገ ወጦች ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህን ተከትሎም በዛፎቹ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል እና ለመቀነስ በዚህ መሰሉ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ ሰዎችን ለማግኘት አሰሳ ጀምረዋል።

ለዚህ አሰሳም ይህን ተግባር የፈጸሙ አካላትን ለጠቆመ እና ላሳየ ሽልማት ይሰጥ ዘንድ አዘዋል።

የዛፎቹን ቅርንጫፎች በመቁረጥ እና ግንዳቸው ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላትን የጠቆመ ግለሰብ 100 የአሜሪካ ዶላር ሸልማት ይበረከትለታል ተብሏል።

እናም ይህን ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ አካላትን ያየ አልያም የሚያውቅ ሰው ካለ ለከተማዋ ፖሊስ ቢደውል እና ቢጠቁም 100 የአሜሪካ ዶላር ያገኛል ነው የተባለው።

የከተማዋ አስተዳዳሪዎች በዛፎቹ ላይ የሚፈጸመው ህገ ወጥ ድርጊት አሳሳቢና በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድም ቁጣን እያስከተለ ነው ይላሉ።

ህገ ወጥ ድርጊት ፈጻሚዎቹ የዛፎቹን ግንዶች መሃል ላይ በመሰንጠቅ የተለያዩ ቅርጾችን ይሰራሉ።

ይህ ደግሞ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከባድ የወንጀል ድርጊት እንደተፈጸመና ምናልባትም እንደሚፈጸም ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

መሰል አጋጣሚዎችም የነዋሪዎች ስነ ልቦና ላይ ተፅዕኖ ስለሚያሳርፉ ይህን መከላከሉ አስፈላጊ ነው ብለዋል የከተማዋ አስተዳዳሪዎች።

 

ምንጭ፦ ኒው ዮርክ ታይምስ