የኒውዚላንድ ዜግነት ያላቸው ጎልማሳ ለዘጠኝ አመታት በአውስትራሊያ የፓርላማ አባል በመሆን አገልግለዋል

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ስኮት ሉድላም ላለፉት ዘጠኝ አመታት በአውስትራሊያ ፓርላማ አባል በመሆን አገልግለዋል።

የ47 አመቱ ጎልማሳ በሃገሪቱ የሚገኘው የአረንጓዴ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር በመሆን፥ በሃገሪቱ ፓርላማ አባልነት የተጠቀሱትን አመታት አሳልፈዋል።

በእነዚህ ጊዜያት ታዲያ ለሶስት የተለያዩ የስራ ዘመናት በፓርላማ አባል በመሆን ቆይተዋል፤ ይህ አገልግሎታቸው እስካለፈው ቅዳሜ ድረስ ቆይቶም ነበር።

ባለፈው ቅዳሜ ግን ከፓርላማ አባልነታቸው ተገለዋል፤ ምክንያቱም የእርሳቸው ዜግነት ኒውዚላንድ እንጅ አውስትራሊያ አልነበረምና።

እናም ለተፈጠረው ነገር ይቅርታ በመጠየቅ ከዚህ ሃላፊነታቸው መገለላቸውን ይፋ አደርገዋል።

ሁኔታው በበርካቶች ዘንድ ግርምትን መፍጠሩ ግን አልቀረም፤ ዘጠኝ አመት ሙሉ ማንነታቸው እንዴት ሳይታወቅ በሚል።

ሉድላም እንደሚሉት እርሳቸው የሶስት አመት ህጻን ልጅ በነበሩበት ጊዜ ወላጆቻቸው ከኒውዚላንድ ወደ አውስትራሊያዋ ፐርዝ ያመራሉ።

ኑሯቸውንም በዚያው ይመሰርታሉ፤ እርሳቸውም ተምረው በአውስትራሊያ ለወግ ማዕረግ በቅተዋል፥ በሂደትም የፓርላማ አባል ሆነው ማገልገል ጀመሩ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አውስትራሊያዊ እንጅ ኒውዚላንዳዊ መሆናቸውን በፍጹም አያውቁም ነበርና በስራቸው ቀጥለዋል።

ወላጆቻቸው ወደ አውስትራሊያ ካመሩ በኋላ ልጃቸውን የጥምር ዜግነት ባለቤት አድርገዋቸዋል፤ እርሳቸው ግን ይህን አያውቁም።

አሁን ላይ የእርሳቸው ዜግነት ኒውዚላንዳዊ እንጅ አውስትራሊያዊ አይደለምና ከሃላፊነታቸው ተገለዋል።

በአውስትራሊያ ህግ መሰረት ደግሞ የፓርላማ አባል ለመሆን ንጹህ አውስትራሊያዊ ዜግነት ብቻ ያስፈልጋል።

በዚህ ሳቢያ ላለፉት ዘጠኝ አመታት በሃገሪቱ ፓርላማ የመቆየታቸው ጉዳይ ግን አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

በትልቁ የመንግስት መቀመጫ በሆነው ፓርላማ ውስጥ አባል የሆነ ሰው አጠቃላይ መረጃ አለመታወቁም ግርምትን ፈጥሯል።

እርሳቸውም ለተፈጠረው ነገር ይቅርታን ጠይቀዋል።

እስከዛሬ የሚያውቁት የአውስትራሊያ ዜግነት እንዳላቸው እንጅ ቤተሰቦቻቸው ያስቀመጡትን የጥምር ዜግነት ባለቤትነት እንዳልነበረም ተናግረዋል።

ለሁሉም የሆነው ነገር ሁሉ አላስፈላጊ ስህተት ነው በማለት በይፋ ይቅርታን ጠይቀው ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል።

የሃገሪቱ ፍርድ ቤትም የእርሳቸውን ምትክ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

 


ምንጭ፦ ዩናይትድ ፕረስ ኢንተርናሽናል