በብሪታኒያ የገመድ አልባ ነጻ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ሰዎች መጸዳጃ ቤት እንዲያፀዱ ግዴታ ተጥሎባቸዋል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሪታኒያ 22 ሺህ ያህል የገመድ አልባ ነጻ ኢንተርኔት (ዋይፋይ) ተጠቃሚዎች ለ1 ሺህ ሰዓታት የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እንዲሰጡ መመሪያ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡

አብዛኞቹ የአገልግሎት መብት እና ግዴታዎችን የማያውቁ በመሆኑ ነው በመመሪያው ላይ በተጠቀሱት ግዴታዎች መሰረት መንገዶችን እና መጸዳጃ ቤቶችችን እንዲያፀዱ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲሰጡ የሚደረገው።

ነጻ የገመድ አልባ ኢንተርኔት አቅራቢ የሆነው ፐርፕል ኩባንያ ነው ተጠቃሚዎቹ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የተዘጋጀው።

ኩባንያው በአጠቃቀም መመሪያው ውስጥ ተጠቃሚዎቹ ባይወዱትም እንኳ በነጻ የገመድ አልባ ኢንተርኔቱ ስለሚጠቀሙት የመረጃ ምንጭ፣ ስለሚከተሏቸው የኢንተርኔት የመፈለጊያ ዝርዝሮች እንዲገልጹ ይጠይቃል።

ፐርፕል የነጻ ኢንተርኔቱን ለማግኘት ተጠቃሚዎች ደንቦችን በቅድሚያ አንብበው ከተስማሙ በኋላ ነው የመጠቀሚያ ኔትዎርክ የሚሰጣቸው ብሏል፡፡

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋቪን ዌልደን እንደተናገሩት፥ ተጠቃሚዎቹ የገመድ አልባ ኢንተርኔት ሲጠቀሙ የሚያገኙት ጥቅም ባሻገር የሚኖርባቸውን ግዴታዎች እንዲገነዘቧቸው ለማድረግ በቀላልና ግልፅ መንገድ ተዘርዝረዋል፡፡

የነጻ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎቹ ከተጣሉባቸው ግዴታዎች መካከል የመዝናኛ ፓርኮች ውስጥ እንስሳትን መንከባከብ፣ ባለቤት አልባ ውሻ እና ድመቶችን ቤት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ለአካባቢያዊ በዓላት ዝግጅት መተባበር፣ በመንገድ ላይ ማስቲካ አለመጣል እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

ፐርፕል ኩባንያ ሙሉ መመሪያውን አንብቦ በውስጡ የተካተተውን ቀልድ ለሚገልፅ ሰው ሽልማት ተዘጋጅቶለታል ብሏል፡፡

እስካሁንም አንድ ሰው ብቻ ሽልማቱን መውሰዱ ነው የተነገረው።

ምንጭ፡- ዘ ጋርዲያን