ላለፉት 32 ዓመታት በየቀኑ ለስድስት ሰዓታት እንደ ሐውልት በመቆም ያገለገለው ህንዳዊ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 7፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ህንዳዊው አብዱል አዚዝ ያለፉትን 32 አመታት እንደ ሃውልት በመቆም አሳልፏል፡፡

የ54 ዓመቱ አብዱል አዚዝ በየዕለቱ በህንድ ህይወት ያለው ሐውልት በመሆን የሚያሳልፈበት ጊዜ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

ግለሰቡ አንድ ቦታ ላይ በሐውልት ቅርፅ በመቆም ሰዎች መተንፈሱን እና መንቀሳቀሱን እስከሚጠራጠሩ ድረስ በቀን ውስጥ ለስድስት ሰዓታት ፀንቶ ይቆያል፡፡

ይህን ተግባር በፈረንጆቹ 19 85 በህንድ ቼናይ በሚገኘው በቪ ጅ ፒ ጎልደን ቢች ሪዞርት በጥበቃ ሰራተኛነት ከተቀጠረ በኋላ ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አዚዝ ከአለቃው ጋር ወደ እንግሊዝ ባመራበት ወቅት፥ የቤኪንግሃም ቤተመንግስት ንጉሳዊ ዘቦች በአንድ ስፍራ ያለምንም እንቅስቃሴ ፀንተው መቆማቸውን ይመለከታል፡፡

ወደ ህንድ ሲመለስም የሪዞርቱ የጥበቃ ሰራተኞች የቤኪንግሃም ንጉሳዊ ዘቦች የሚሰሩትን ተግባር እንዲለማመዱ የሶስት ወር ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡

በዚህ ስልጠናም አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ መመገብ፣ መጠጣት እና ማሽተትን በሚገልፅ መንገድ አተነፋፈስን መከተል አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡

ዝንብ በፊት ገፅታቸው ላይ ቢያርፍባቸውም እንኳ ማባረር አይችሉም፡፡፡

ለአራት ሰዓታት በየቀኑ ያለምንም እንቅስቃሴ እንደሐውልት በመቆም በሚሰጠው ስልጠናም አብዱል አዚዝ ብቁ ሆኖ ተገኘ፡፡

Statue-Man.jpg

ሐውልቱ ሰው የተባለው አዚዝ በሪዞርቱ ውስጥ ከጥበቃ ሰራተኝነት ህይዎት ወዳለው ሐውልትነት ስራውን ሲቀይር ግን መወላወሉን ተናግሯል፡፡

ሆኖም የሪዞርቱ ደንበኞች እንዲጎበኙት በየቀኑ ለስድስት ሰዓታት ህይወት ያለው የሰው ሐውልት ሆኖ በማገልገል ላለፉት 32 ዓመታት አገልግሏል፡፡

አዚዝ ሰዎች ቀልድ ሲያወሩት አይስቅም፣ ሰዋዊ እንቅስቃሴ አያደርግም፣ ዓይን ለዓይን እየተያዩ ሲጠቅሱት እና ህይወት ያለው ሰው መሆኑን የሚያሳውቁ ድርጊቶች ሲፈፅሙበትም ምንም ዓይነት ለውጥ አለማሳየቱ ደግሞ ብዙዎችን አስደምሟል፡፡

ዓይኖቹም ለስድስት ሰዓታት ያህል አይጨፈኑም፤ አይርገበገቡም፡፡

Statue-Man5.jpg

አብዱል አዚዝ ፅኑ ህይወት ያለው ሐውልትነት የተማመነው የቪ ጅ ፒ ቢች ሪዞርት ከሚጎበኙት መካከል አዚዝን እንዲንቀሰቀቀስ የሚያደርጉ ሰዎች ካሉ 155 ዶላር እንደሚሸልም ቃል እየገባ ጎብኝዎች ሲሞክሩ ቢውሉም እስካሁን የተሳካለት ሰው አልተገኘም፡

ይህ ደግሞ ለሪዞርቱ አንድ የገቢ ምንጭ ሆኗል።

አንዳንድ ጊዜ ህጻናት አዚዝን ለመምታት እና ለመውጋት ሲሞክሩ በአቅራቢያው የሚገኙ የጥበቃ ሰራተኞች ይከላከሉለታል ተብሏል፡፡

አዚዝ ይህን ስራ እንደጀመረ አካባቢ ጥሩ ስሜት ቢኖረውም፥ አሁን ላይ ግን ለረዥም ጊዜ ያለምንም እንቅስቃሴ አንድ ቦታ ላይ እንደ ሐውልት መቆሙ ጭንቀት እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡

Statue-Man6.jpg

ደሙ በሰውነቱ ውስጥ በተገቢው ሁኔታ እንደማይዘዋወር እና ለጤና ቀውስ እንዳጋለጠውም ጠቁሟል፡፡

የቤኪንግሃም ቤተመንግስት ንጉሳዊ አጃቢዎች በየሁለት ሰዓቱ የሚፈራረቁ ሲሆን፥ አዚዝ ግን ለስድስት ሰዓት የሚተካለት ሰው የለም፡፡

ወደ ቤቱ ሲመለስ ዮጋ እና ሌሎችን አካላዊ እንቅስቃሴዎች በማድረግ፣ የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ እንደሚያሳልፍም ነው የገለፀው፡፡

አብዱል አዚዝ ላለፉት 32 ዓመታት በሐውልትነት ሲያገልግል የህንድ፣ የማሌዥያ፣ የሲንጋፖር እና የሌሎችም ሀገራት ታዋቂ ሰዎች ጎብኝተውታል፡፡

ለዚህ ፈታኝ ስራው ከሪዞርቱ በየወሩ የሚያገኘው ገቢ ደግሞ 10 ሺህ ሩፒ ብቻ ነው፡፡

ገንዘቡ ለቤተሰቡ የዕለት ወጪ በቂ ቢሆንም ለልጆቹ የነገ ሕይወት የሚያወርሰው እንደሌለም ይጠቅሳል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጡረታ ለመውጣት ማቀዱን ነው የጠቆመው አዚዝ፥ በእርሱ ቦታ የሚተኩ አምስት እጩዎች ቀርበው አንዱ ብቻ መስፈርቱን አሟልቶ በመገኘቱ ስልጠና እየወሰደ ነው ብሏል፡፡

አዚዝ ከጤና ስጋት ውጭ ስራውን በጣም እንደሚወደው ነው የተናገረው፡፡

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-odditycentral.com

በምህረት አንዱዓለም