በአሜሪካዋ ሚዙሪ ሌቦች አነስተኛ ቤት ከቆመበት ሰርቀዋል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሌባ ቤት ሰብሮ ሲሰርቅ እንጂ አንድ የቆመን ቤት ሙሉ በሙሉ ነቅሎ መስረቅ የተለመደ ነገር አይደለም።

ከአሜሪካዋ ሚዙሪ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ግን ሌቦች አንድ አነስተኛ ቤት ከቆመበት ነቅለው ሰርቀዋል ይለናል።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው፥ ሊሳ ስቱብልፊልድ የተባለችው የሚዙሪ ከተማ ነዋሪ አነስተኛ ተንቀሳቃሽ ቤቷን በአካባቢው ለሚከበር ፌስቲቫል ብላ አካባቢው ላይ ታቆማለች።

ፌስቲቫሉ በሚከበርበት ቅዳሜ እለት በጠዋት ወደ ስፍራው ስትመለስ ግን ቤቱን ከቦታው ላይ ማግኘት አልቻለችም ነበር።

በሁኔታው የተገረመችው ሊሳ የሆነ ሰው ቤቱን ሆን ብሎ እንደሰረቀባት መጠራጠሯንም ተናግራ፥ ቤቷ እንደተሰረቀባትም ለፖሊስ ታመለክታለች።

ሊሳ የተሰረቀባት ቤት አራት ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን፥ የትልቅ ቤት ቅርጽ ይዞ የተሰራ ነው።

ቤቱንም ተንቀሳቃሽ የአልባሳት መሸጫ አድርጋው ነበር የምትጠቀመው።

ፖሊስ ሊሳ ቤቷን መሰረቋን ካመለከተችበት በቀጣይ ቀን ቤቱን ማግኘት ችለዋል።

ከቤቱ ስርቆት ጋር በተያያዘ ግን አስካሁን በቁጥጥር ስር የዋለ ተጠርጣሪ የለም ተብሏል።

ምንጭ፦ www.nytimes.com