በውሃ ውስጥ ከ5 ሰዓት በላይ የቀጥታ የሬዲዮ ፕሮግራም ያስተላለፈው ጋዜጠኛ የዓለም ክብረወሰን ያዘ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)በውሃ ውስጥ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን ለረጅም ሰዓት የቀጥታ የሬዲዮ ፕሮግራም ያቀረበው ጋዜጠኛ በዓለም የድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍሯል፡፡

ስቱ ቶላን የ104 ነጥብ 8 የሬዲዮ ጣቢያ4 ጋዜጠኛ ሲሆን ፥በዱባይ ወደሚገኘው አትላንቲስ ደሴት ሪዞርት ያመራል፡፡

በባህር ዳርቻ ሪዞርቱ ውስጥ ቢያንስ 3 ሚሊየን ጋሎን የውሃ ክምችት ያለው አነስተኛ ባህር አለ፡፡

በዚህ ባህር ውስጥም የቀጥታ የሬዲዮ ስርጭቱን በመጀመር ለተከታታይ 5 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ከ25 ሰከንድ ያለማቋረጥ ያቀርባል፡፡

ጋዜጠኛ ቶላን"በህይወቴ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት መሳተፌ ደስተኛ እንድሆን ቢያደርገኝም አሁን በባህር ውስጥ ሆኜ የቀጥታ የሬዲዮ ፕሮግራም ሳዘጋጅ እና በድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሜ መስፈሩ ልዩ አግራሞትን ፈጥሮብኛል" ነው ያለው፡፡

"የስራ ባልደረቦቼ ፈታኙን የውሃ ውስጥ የቀጥታ ስርጭት ለማስተባበር ባደረጉት ብርቱ ጥረት ህልማችንን እውን አድርገናል" ብሏል ቶላን፡፡
ቶላን ከዚህ በፊት የነበረውን ክብረ ወሰን በ1 ሰዓት አሻሽሎታል፡፡

ጋዜጠኛው በውሃው ውስጥ ለአድማጮቹ ሙዚቃ ሲጋብዝ ፥በስልክም አስተያየት እየተቀበለ እና ፕሮግራሞቹን እያስኬደ ከ5 ሰአት በላይ በቀጥታ ስርጭት ቆይቷል፡፡

ፕሮግራሙን በውሃ ውስጥ በሚያቀርብበት ወቅት በ65 ሺህ የባህር ውስጥ እንስሳት ተከብቦም ነበር፡፡

ስድስት የውሃ ውስጥ እውቅ ዋናተኞች ቶላን የኦክሲጅን እጥረት እንዳያጋጥመው እና ፕሮግራሙ የተሳካ እንዲሆን፥ 11 ጊዜ ወደ ጊዜያዊ የሬዲዮ ጣቢያው እየተመላለሱ የሚፈለገውን ለማሳካት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

እነቶላን የውሃ ውስጥ የቀጥታ የሬዲዮ ፕሮግራም ስርጭታቸውን ለረጅም ሰአታት አቅርበው የዓለም ክብረወሰንን ከተቀዳጁ በኋላ የአትላንቲስ ሪዞርት ተወካይ ራቪኒ ፔሬራ በአስተያየታቸው፥ ከእለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ያጋጥማል ብለን የማናስበው አስገራሚ ነገር ዛሬም በዚህ ስፍራ ተከሰተ ብለዋል፡፡

ምንጭ፡-ዩ ፒ አይ