ያሰበው ያልተሳካለት ግለሰብ ሲኒማ የጋበዛት ጓደኛው የመግቢያ ዋጋውን እንድትከፍል ከሷታል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) አሜሪካዊው ጎልማሳ ፊልም አብረው እንዲመለከቱ የጋበዛት ጓደኛውን ፊልሙ በሚታይበት ጊዜ በርካታ መልዕክቶችን በሞባይልሽ ተለዋውጠሻል በማለት የመግቢያ ትኬቱን ዋጋ እንድትመልስለት ከሷታል።

የቴክሳሱ ብራንደን ቬዝማር ለፊልም መመልከቻ የከፈልኩት 17 ነጥብ 31 የአሜሪካ ዶላር ይመለስልኝ ሲል ነው ክሱን ያቀረበው።

የ37 አመቱ ጎልማሳ ለኦስቲን አሜሪካን ስቴስማን ጋዜጣ እንደገለፀው፥ በኢንተርኔት አማካኝነት ካገኛት ሴት ጋር "Guardians of the Galaxy, Vol. 2" የሚል ፊልም ለመመልከት ባለፈው ሳምንት ተያይዘው ያመራሉ።

ስሟ ያልተጠቀሰው የ35 አመቷ የቬዠማር ጓደኛ ግን ፊልሙን መከታተል በመተው በሞባይሏ መልዕክቶችን መላላኳን አላቆም ትላለች።

ቬዝማር እንደሚለው ይህን ድርጊቷን እንድታቆም ደጋግሞ ቢነግራትም አሻፈረኝ አለች።

ይባስ ብሎም ጎልማሳውን ብቻውን ትታው ፊልሙን አቋርጣ ወጥታ በዚያው ትቀራለች።

በዚህ ሁኔታዋ የተበሳጨው ቬዝማር ከቀናት በኋላ የትኬት ዋጋውን እንድትመልስ እንደጠየቃት ተናግራለች።

ይሁን እንጂ እሱ ወዶ እና ፈቅዶ የጋበዘኝ ነገር በመሆኑ ልመልስለት አልችልም ብላለች።

ቬዝጋር ግን ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት እንደሚያገኝ ተስፋ አድርጓል።

 

 

ምንጭ፦ አሶሼትድ ፕሬስ