ጠጥቶ ሲያሽከረከር የነበረው ግለሰብ መኪናው ለፖሊስ ባደረገችው ጥቆማ ለእስራት ተዳርጓል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠጥቶ ሲያሽከረከር የነበረው ግለሰብ በመንገድ ላይ የተጋጨ ሲሆን፥ ይህን አደጋ ያስተናግደችው ተሸከርካሪም በተገጠመላት ዘመናዊ የመልዕክት ማድረሻ ቴክኖሎጂ ለፖሊስ ሪፖርት አድርጋለች።

ነገሩ የሆነው እንዲህ ነው በሰሜናዊ አየርላንድ አንድ ፎርድ ፌስታ መኪና ጠጥቶ በሚያሽከረከራት ግለሰብ መሪውን በአግባቡ ባለመጠቀም ምክንያት አደጋ ይደርስባታል፡፡

በዚህ ጊዜም ተሸከርካሪዋ በተገጠመላት የአደጋ ማሳወቂያ ዘመናዊ ስልክ የድረሱልኝ ጥሪ ለማድረግ ወደ ፖሊስ ትደውላለች፡፡

የሰሜን አየርላንድ የፖሊስ መስሪያ ቤት አባላትም አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ በማቅናት ሁኔታውን ይመረምራሉ፡፡

ፖሊሶች ለአደጋው መፈጠር ዋነኛው ተጠያቂ የአሽከርካሪው ከመጠን በላይ ጠጥቶ መገኘት መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡

ግለሰቡም ከህግ ከተወሰነው የአልኮል መጠን በላይ ጠጥቶ በመገኘቱ ወደ ጊዜያዊ ማረፊያ ተወስዶ ቅጣቱን እየተጠባበቀ ነው፡፡

የአካባቢው ፖሊስ መስሪያ ቤትም በመግለጫው ተሸከርካሪዎች ዘመናዊ  እየሆኑ መምጣታቸውን በመጠቆም፥ አደጋ ሲከሰት ውዲያውኑ ለፖሊስ የሚያሳውቁበት የቴክኖሎጂ ውጤት የተገጠመላቸው ተሸከርካሪዎች ደግሞ የፖሊስን ስራ በማገዝ ትልቅ ሚና አላቸው ብሏል፡፡

በተሸከርካሪዎች ላይ የሚገጠሙትና በራሳቸው ጊዜ አደጋን ለፖሊስ የሚያሳውቁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ጠጥቶ ለሚያሽከረከር ሰው ጠላት እና አጋላጭ መሆናቸውንም ፖሊስ ጠቅሷል፡፡

ግዑዝ አካል የሆነው ተሸከርካሪያቸው እስከሚታዘባቸው እና ወንጀላቸውን የሚያጋልጥ ጥቆማ እስኪሰጥባቸው ድረስ፥ አደጋ የሚያደርሱ ሰዎች ቢቻል አልኮል ከመጠጣት ቢቆጠቡ ካልቻሉም ደግሞ ከመጠን ባያልፉ ተገቢ መሆኑን ፖሊስ መክሯል፡፡

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፡- ቢቢሲ