አንድ የቻይና ኩባንያ ከክብደታቸው 1 ኪሎግራም ለሚቀንሱ ሰራተኞቹ 15 ዶላር እየሸለመ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ኩባንያ ሰራተኞቹ ከመጠን ያለፈ ክብደታቸውን እንዲቀንሱ እያበረታታ ሲሆን፥ ከክብደታቸው ላይ ግማሽ ኪሎ ግራም በቀነሱ ቁጥር 15 የአሜሪካ ዶላር ያበረክትላቸዋል፡፡

በሀገሪቱ ዢያን ከተማ የጂንግቲን የኢንቨስትመንት አማካሪ ድርጅት ሃላፊው ዋንግ ዡባኦ ሰራተኞቻቸው ክብደታቸውን እንዲቀንሱ ለማበረታታት አዲስ የሽልማት ፕሮግራም ነድፈዋል፡፡

የድርጅቱ ሰራተኞች ከክብደታቸው አንድ ኪሎ ግራም በቀነሱ ቁጥር 200 ዩዋን ወይም 15 የአሜሪካ ዶላር ሽልማት ያገኛሉ፡፡

የክብደት ቅነሳ አዲሱ የቅስቀሳ ዋና ዓላማም ሰራተኞች ጤናማ፣ ጥሩ ተክለቁመና እና ቅርፅ እንዲኖራቸው ለማድረግ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የድርጅቱ ሃላፊ ዋንግ ዡባኦ ይህን ሃሳብ ያመነጩት እርሳቸው እና ሰራተኞቻቸው ብዙ ጊዜ ተቀምጠው ስለሚሰሩና እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ለውፍረትና ለክብደት መጨመር ስለተጋለጡ ነው፡

ለውፍረት የሚጋብዝ አመጋገብን ማዘውተርም ለሰራተኞቻቸው ከመጠን ላለፈ ክብደት መጨመር ሌላው ምክንያት ሆኖ አግኝተውታል ሃላፊው፡፡

ይህን ተከትሎም አዲስ የክብደት መቀነስ እንቅስቃሴን ይፋ በማድረግ ክብደት ለሚቀነሱ ሰራተኞች የሽልማት መርሃ ግብር ተግብረዋል፡፡

ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የክብደት ቅነሳ መርሃ ግብሩ፥ ከተቋሙ ሰራተኞች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በአንድ ወር እንቅስቃሴ ብቻ ጥሩ የክብደት ቅነሳ ማሳየታቸው ተመዝግቧል፡፡

weight-loss-for-cash2-750x450.jpg

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ለውፍረትና ለክብደት መጨመር የማያጋልጡ አመጋገቦችን ማዘውተር የተቋሙ ሰራተኞች ባህል እየሆነ መጥቷል ነው የተባለው፡፡

ከሰራተኞች መካከል ወጣቷ ዡ ዌይ ባለፉት ሁለት ወራት 20 ኪሎግራም ክብደት መቀነሷን ጠቅሳ፥ በዚህ እንቅስቃሴዋም 2 ሺህ ዩዋን ወይም የ300 የአሜሪካ ዶላር ሽልማት ማግኘቷን ተናግራለች፡፡

ወጣቷ ዡ ዌይ በየዕለቱ ወደ ስፖርት ማዘውተሪዎች እንደምትሄድና ጂምናዚየም እንደምትሰራ፥ እለታዊ አመጋገቧንም ማስተካከሏ ለክብደት መቀነስ እንደረዳት ጠቅሳለች፡፡

ተቋሙ ግማሽ ኪሎግራም ለሚቀንሱ ሰራተኞችም 100 ዩዋን ሽልማትን ያዘጋጀ ሲሆን፥ ሽልማቱ የሚበረከትላቸው ግን ከመጠን ያለፈ ክብደታቸው ላይ ቢያንስ ሶስት ኪሎ ግራም መቀነሳቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡

ድርጅቱም በዚህ እንቅስቃሴው ጤናማ የሰው ሃይልን ሲገነባ ሰራተኞች ደግሞ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሆኗቸዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ማማከር ድርጅቱ ሃላፊ ዋንግ ዡባኦ ለሰራተኞቻቸው የሚያደርትን የሽልማት ፕሮግራም፥ ለራሳቸውም ክብደታቸውን በቀነሱ ቁጥር በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ከፋይናንስ ክፍላቸው እንደሚበረከትላቸው ተናግረዋል፡፡

በቻይና ውፍረት እና ከመጠን በላይ ክብደት የዜጎች አስጊ የጤና ቀውስ መሆኑን ቀጥሏል፤ በ2030 የፈረንጆች ዓመትም ከአራት ቻይናዊ ልጆች መካከል አንዱ ከመጠን ላለፈ ክብደት እንደሚጋለጥ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-ኦዲቲ ሴንትራል