ስምንት እግር መሳይ ትርፍ የሰውነት አካል ይዞ የተወለደው ህጻን በቀዶ ህክምና ተወግዶለታል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢራቅ ውስጥ ስምንት እግር መሳይ ትርፍ አካላትን ይዞ የተወለደ ህጻን በከፍተኛ የቀዶ ህክምና ሂደት ትርፍ እግሮቹ ተወግደውለታል፡፡

የሰባት ወር እድሜ ያለው ህጻን ካራም አልፎ አልፎ የሚደረግ ከፍተኛ እና ልዩ ህክምና ነው የተደረገለት ተብሏል፡፡

በካራም የተከሰተው የብዙ እግር መሳይ አካላት ሊፈጠር የሚችለው በእናት ማህፀን ውስጥ ሁለት ፅንሶች በስነሕይወታዊ ሲጣመሩ ነው፡፡

ይህም ክስተት ፖሊመሊያ የሚባል ሲሆን በማህፀን ውስጥ ሁለት ፅንሶች፥ ተጣምረው ወይም አካላቸው ተገናኝቶ ሲፈጠሩ እና የተዛባ እድገት ሲያሳዩ በሂደትም አንደኛው ፅንስ እድገቱን ሲያቆም ህጻናት ሲወለዱ ብዙ እግር መሳይ አካላትን ይዘው እንዲወለዱ ያደርጋል፡፡

ካራምም በዚህ መልኩ ስምንት እግር እና እጅ መሳይ አካላትን ይዞ ነው የተወለደው፡፡

8_limb4.jpg

ወላጆቹም ወደ ህንድ ለከፍተኛ ቀዶ ህክምና ይዘውት የሄዱ ሲሆን፥ በህክምናውም ሁለት እጆቹ እና ሁለት እግሮቹ ሲቀሩ ሌሎች ትርፍ እግር እና እጅ መሳይ የሰውነት ክፍሎቹ ተወግደውለታል፡፡

ሶስት ደረጃዎችን ያለፈ፣ ከፍተኛ ድካምን የጠየቀ የመጀመሪያው ዓለም አቀፋዊ የህክምና ሂደት ነው ተብሏል፡፡

ካራም ለወላጆቹ የመጀመሪያ እና ብቸኛ ልጅ ሲሆን አባቱም አሁን ልጄ ጤነኛ እና መደበኛው የሰው ልጆች የአካል ቅርፅ እንዲኖረው በመደረጉ ደስ ብሎኛል ብለዋል፡፡

8_limb2.jpg

ካራም ህንድ ውስጥ በሚገኘው ወደ ጃይፔ ሆስፒታል ለቀዶ ህክምና ሲወሰድ የሁለት ሳምንት እድሜ ነበረው፤ ወደ ቤቱ ሲመለስ ግን እድሜው ሰባት ወር ሆኗል ተብሏል፡፡

የእግሩ የአበቃቀል ችግር፣ አጭር እና ረጅም መሆን ቀዶ ህክምናውን አስቸጋሪ እና ረጅም ጊዜ እንዲወስድ አድርጎታል ብሏል ሆስፒታሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-www.dailymail.co.uk