እግር ኳስን ለመታደም ስታዲየም ያመሩ ስምንት ሴት ኢራናውያን በቁጥጥር ስር ውለዋል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራናውያን ጠንካራ ሃይማኖታዊ ህጎችን ከሚተገብሩ ሃገራት መካከል ይጠቀሳሉ።

በዚያች ሃገር ሴቶች ወደ እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች ገብተው ኳስ ጨዋታዎችን ይታደሙ ዘንድም የተከለከለ ነው።

በመዲናዋ ቴህራን በሚገኘው የአዛዲ ስታዲየም እየተደረገ የነበረን ጨዋታ ለመታደም ወደዚያው ያመሩ ሴቶችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በወቅቱ ኤስቴግላል እና ፔርሴፖሊስ የተሰኙ ሁለት ክለቦች ጨዋታቸውን ያደርጉ ነበር።

የእግር ኳስ ፍቅር ያላቸው ሴቶች ወደ ስታዲየም ለመግባት እና ጨዋታውን ለመከታተል በሚል አለባበሳቸውን በመቀየር ራሳቸውን ወንድ በማስመሰል ወደ ስታዲየሙ ያመራሉ።

እነዚሁ ሴቶች ስምንት ሲሆኑ ሁለቱ በስታዲየሙ መግቢያ በር ላይ በጸጥታ አካላት ሲያዙ ስድስቱ ግን ጨዋታውን እየተከታተሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሴቶቹ አለባበሳቸውን የቀየሩት ስታዲየም ገብቶ እግር ኳስ ጨዋታ መከታተል የማይቻልና የተከለከለ በመሆኑም ነበር።

ይሁን እንጅ ያሰቡት ሳይሳካ በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ በቀጣይም ህጉን በመተላለፋቸው ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።

የቴህራን አስተዳደር የጸጥታ ክፍል ሃላፊው፥ ይህን መሰሉ ድርጉት በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ በስታዲየሙ ያለው አጠቃላይ ድባብ ለሴቶች የማይመች በመሆኑ ወደዚያ ማቅናታቸው ለእነርሱ ሲባል መደረጉንም ይገልጻሉ።

እግር ኳስን ከወደዱም ቤታቸው ቁጭ ብለው መመልከት የሚችሉበት አማራጭ መኖሩን ገልጸዋል።

በሃይማኖታዊ ስርዓት በመንፈሳዊ መሪ የምትመራው ኢራን፥ ከስታዲየም የእግር ኳስ ጨዋታ መከታተል ባለፈም በአደባባይ ሴት ልጅ ብስክሌት ማሽከርከሯን ትከለክላለች።

ምክንያቱም እነርሱ ብስክሌት ሲያሽከረክሩ ሁኔታው የወንዶችን ትኩረት ይስባልና ይህ አግባብ አይደለም ይላል የሃገሪቱ ህግ።

ከዚህ ባለፈም በሶሻል ሚዲያዎች ላይ ፎቶ ግራፍ ሲለቁ ያለ ራስ ክንብንብ መሆን እንደሌለበትም የቴህራን ሃይማኖታዊ ህግ ይደነግጋል።

በተጨማሪም ምንም ያክል ደስታና ስሜትን መግለጽ ብትፈልግ አንድ ኢራናዊ ሴት በኢንተርኔት እያንጎራጎረች ተንቀሳቃሽ ምስል መልቀቅ በህግ ያስቀጣታል።

 

 

 

ምንጭ፦ ደይሊ ሜይል