አንድ የፖሊስ አዛዥ ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከሩ በራሱ ላይ የጥፋት ቅጣት ሰጥቷል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦክላሆማ ግዛት ውስጥ የፖሊስ አዛዥ የሆነው ግለሰብ ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር ጥፋት ራሱን መቅጣቱን አስታውቋል፡፡

ሆኖም የካሜራ ቪዲዮ ላይ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከሩን ካረጋገጠ በኋላ መስጠቱ አወዛጋቢ ሆኗል፡፡

ምክንያቱም በፍጥነት መንገድ ካሜራ የተቀረፀው የቪዲዮ ማስረጃው ባይኖር፥ አዛዡ ራሱን ይቀጣ ነበር ወይ የሚለውን በእርግጠኝነት መናገር ስለማይቻል ነው ተብሏል፡፡

በርካታ ሰዎችም የፖሊስ አዛዡ እንዴት የፍጥነት ወሰን ጥሶ ያሽከረክራል የሚል ቅሬታን በፌስቡክ ገጻቸው መቀባበል ጀመሩ፡፡

ይህን ተከትሎም ማንኛውም ሰው ለጥፋቱ መቀጣት እንዳለበት ሁሉ እኔም ጥፋተኛ ስለሆንኩ መጠየቅ ይገባኛል፤ ይህም በመሆኑ በራሴ ላይ ቅጣት አስተላልፌያለሁ ነው ያለው አዛዡ፡፡

ፖሊስ አዛዥ ጀስቲን ቡርች ከተቀመጠው የፍጥነትነ ልክ በላይ በማሽከርከሩ ጥፋት ማጥፋቱን አምኗል፤ ለዚህ ስህተቱም ልባዊ ቅርታ ጠይቋል፡፡

የፍጥነት ወሰኑ 50 ማይል በሰዓት በሆነበት መንገድ ወሰኑን ተላልፎ ከ75 እስከ 80 ማይሎችን በሰዓት እንደነዳም አምኗል፡፡

ፖሊስ አዛዡ በዚህ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ጥፋትም 300 የአሜሪካ ዶላር ቅጣትን በራሱ ላይ አስተላልፏል፡፡

ምንጭ፡-ደይሊ ሜይል